ሀገሬ ቲቪ

ዕለቱን ከታሪክ- የጠፈር ተቀናቃኞቹ የህብረት ሁነት

ዩናይትድ ስቴትስ እና ሩስያ ለአመታት በጠፈር ፕሮግራም በከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ነበሩ። እነዚህ በጠፈር እቅድ ፉክክር ውስጥ የነበሩት ሃገራት ሩብ ክፍለ ዘመን በፊት በዛሬዋ ዕለት የጋራ የጠፈር ተልዕኮን ማድረግ ችለዋል።

ጊዜው 1987 ዓ.ም. ነው። የአሜሪካ የጠፈር መንኮራኩር መርከብ እና የሩስያ የጠፈር ተቋም ሚር ለአንድ ጉዳይ ተጣምረዋል። በሰው የተሰራው ትልቅ ሳታላይትን በመሬት ዙሪያ እንዲሽከረከር ለማድረግ። ይሄው በጠፈር ፕሮግራም ተቀናቃኝ የሆኑት ሃገራት ታሪካዊ የትብብር ሁነት በአሜሪካ የጠፈር ተልዕኮ ታሪክ መቶኛው ነው።

በጊዜው የናሳ ኃላፊ የነበሩት ዳንኤል ጎልዲን ክስተቱን የአሜሪካ እና ሩስያ የትብብር እና የወዳጅነት አዲስ ምዕራፍ ሲሉ ነበር የገለጹት።

ሚሊዮኖች በቴ.ቪ. መስኮት እየተከታተሉት በ1987 ዓ.ም. ሰኔ 20 አትላንቲስ ከፍሎሪዳው የኬኔዲ ጠፈር ማዕከል ወደ ጠፈር ተመነጠቀች።

ከሁለት ቅናት በኋላ በዛሬዋ እለት ታዲያ አትላንቲስ እና የያዘቻቸው ሰባት ጠፈርተኞች በ394 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ወደ ሩስያው የጠፈር ተቋም ሚር(Mir) ቀረቡ።

አትላንቲስን ባዩ ቅጽበት በሚር የነበሩት ሶስት ጠፈርተኞች የሩስያን ባህላዊ ሙዚቃ በማስተላለፍ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋቸዋል። ከሁለት ሰአታት በኋላ የመንኮራኩሯ በረራ አዛዥ ሃላፊ ሮበርት ሁት ጊብሰን የመንኮራኩሩን ሥራ ወደ ጠፈር ጣቢያው አቅጣጫ አዘዋወረ።

እረፍታውን ከሚር ላይ ለማድረግ ጊብሰን 100 ቶን የምትመዝነውን አትላንቲስ 123 ቶን ከምትመዝነዋ ሚር ማስጠጋት ነበረበት። ከታሰበው ጊዜ በፈጠነ አኳኋን አትላንቲስ እና ሚር በህብረት በመጣመር በጠፈር ላይ የምንጊዜም ትልቁን መንኮራኩር በምህዋር ላይ መፍጠር ችለዋል።

ይሄው በጠፈር ላይ የመጣመር ሁነት በ1967 አሜሪካ እና ሩስያ በጋራ ካደረጉት ቀጥሎ ሁለተኛው ነው። በመጀመሪያው የአሜሪካዋ አፖሎ ካፕሱል ከሩስያዋ መንኮራኩር ሶዩዝ ጋር በጠፈር ላይ ለአጭር ጊዜ እንዲጣመሩ ተደርጓል።

በሁለተኛው የአትላንቲስ እና የሚር ጥምረት የአትላንቲስ የበረራ ኃላፊ ጊብሰን እና የሚር ኃላፊ ቭላድሚር ዴዙሮቭ በመጨባበጥ ይሄንንው ታሪካዊ ሁነት ተጋርተዋል።

ሁለቱ የጠፈር እቅድ ተቀናቃኞች የአሜሪካ እና ሩስያ የህብረት ስኬት። በጠፈር ላይ የስጦታ ልውውጡ ቀጠለ። የአትላንቲስ ጠፈርተኞች ቸኮሌት፣ ፍራፍሬ እና አበባ ሲያቀርቡ የሚር ጠፈርተኞች ደግሞ የሩስያን ባህላዊ የእንኳን ደህና መጣችሁ ስጦታዎችን፣ ዳቦ እና ጨውን አቀረቡ።

ወደ መሬት ከመመለሷ አስቀድሞ አትላንቲስ ለአምስት ቀናት ከሚር ጋር በምህዋር ላይ በጥምረት ቆየች። ሁለት አዳዲስ የሩስያ ጠፈርተኞችን በጠፈር ተቋሙ በመተው ወደ መሬት። የናሳ ከሚር ጋር የተያያዘው ፕሮግራም 11 ተልዕኮዎችን ቀጥሏል።

ይሄውም ለአለም አቀፉ የጠፈር ተቋም ግንባታ የራሱን ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይሄው የሁለቱ ሃገራት የትብብር የጠፈር ፕሮግራምም ትልቅ የታሪክ ክስተት ተደርጎ ይታሰባል።

በአብርሃም በለጠ
2022-06-29