በዓለማችን ላይ ኑሮን ለማቅለል ይረዳሉ ተብለው የተፈጠሩት ነገሮች በጠቅላላ መነሻቸው አለማስቻል ወይም ችግር ነው።
ስንቅ ቋጥሮ ወራትን አልያም ዓመታትን በመንገድ ላይ ማሳለፍ የለም።
ዛሬ ረዝም ርቀት መጓዝ የሰከንዶች አለፍ ካለም የሰዓታት ጉዳይ ብቻ ነው።
ከአንዱ ጫፍ ያለን መልዕክት ለመስማት እንደቀድሞዎቹ ዘመናት ግዜያትን መጠበቅ የለም።
በእጅ በምኛዛቸው ስልኮች በሰኮንዶች ውስጥ በእጃችን ላይ ሁሉም ነገር ይደርሳል።
ይህንን ያሳየን ዘመን አሁን ደግሞ ውሃ የማያስገባ ቤትን ተዋወቁ ሳይለን አልቀረም።
የዚህ መላ ባለቤት ጃፓን ነች።
ከወደ ጃፓን ኢቺጆ ኮሙተን የተባለ የቤት አልሚ ኩባንያ በጎርፍ ለምትቸገረዋ ሀገሩ ሁነኛ መላን ዘይዷል።
ጎርፍን መቋቋም የሚችል ቤት ሰርቶ ይፋ አድርጓል።
ጃፓን በተፈጥሮ አደጋዎች ደጋግማ የምትጎበኝ ሀገር ነች።
በጎርፍ ሳቢያ በየዓመቱ ዜጎቿን ታጣለች።
በጎርፍ ሳቢያም ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥርም እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በተለይ የክረምቱን መግባት ተከትሎ የሚጥለው ዝናብ ቀጥሎም የሚከሰተው ጎርፍ የሰዎችን መኖሪያ ጠርጎ ደብዛውን ያጠፋዋል።
ብርቱዎቹ ጃፓናውያን ግን ለችግሩ እጅ አልሰጡም አዲስ ቤት ተዋወቁ ብለውናል።
ቤቱ ከተለመደው የቤት አሰራር የሚለይ አይመስልም።
ነገር ግን በቦታው ዝናብ መጣል ሲጀምር እና ጎርፍ ሲከሰት ልዩነቱ በግልጽ መታየት ይጀምራል።
ቤቱ በውጪ ያለውን ዝናብ እና ጎርፍ ወደ ውስጥ እንዳይገባ ከማድረግም አልፎ አደገኛ ጎርፍ ቢከሰት እንኳን ባለበት በውሃው ላይ እንደ ጀልባ ተንሳፎ መቆየት የሚችል ነው።
ቤቱ ከዚህ ቀደም እንደምናውቃቸው አይነት መሰረቱን አፈር ቆፍረው ያፀኑት አይደለም።
እንደው ቀለል ባሉ ደህነኛ የቤት መገንቢያ መሳሪያዎች የተገነባ ሲሆን በአራቱም የቤቱ ማዕዘናት ደግሞ ከመሬት ስር ጠልቀው በተተከሉ ችካሎች ታስሮ ይገኛል።
ችካሎቹ በኃይል የሚመጣ ጎርፍ ቤቱን ወስዶ መድረሻ እንዳያሳጣው የሚይዙ ናቸው ተብሏል።
በተለይ ጎርፍ ወደ ቤት ውስጥ እንዲገባ ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ ዋነኞቹ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ናቸው።
ጠቢባኑ የጃፓን ቤተሰሪዎች ሁነኛ መላን ዘይደውለታል።
ፍሳሽ ከቤት ውስጥ ሲወጣ መከፈት የሚችል ከውጪ ላለው ጎርፍ ኝ ክርችም ብሎ መዘጋት የሚችል ፈጠራን ተጠቅመዋል።
ከመሬት በላይ እስከ 5 ሜትር ድረስ መንሳፈፍ የሚችሉት እነዚሁ ቤቶችውሃው በበሮቻቸው ስር እንዳይገቡ የሚያስችል ፈተራ የታከለባቸው ናቸው።
ታዲያ ይህ አይነቱ ቤት ምን ያህል ያስከፍለኝ ይሆን ለሚለው ቤተሰሪዎቹ ይህንን ብለዋል።
አስቀድመው ቤት ለመገንባት ከሚያወጡት ወጩ 5,700 ዶላር ያህል ያስጨምሮታል ብለዋል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-06-29
