ሀገሬ ቲቪ

ዕለቱን ከታሪክ - የኮንጎ ነጻነት

ኮንጎ በመካከለኛው አፍሪካ የምትገኝ በማዕድን የበለጸገች ሀገር ነች። ይህችው ለአለም አልማዝ እና ሌሎች ማእድናትን በማቅረብ የምትታወቀዋ ሀገር ለግማሽ ክፍለ ዘመን በቤልጅየም ቅኝ ግዛት ስር ቆይታለች። ሀገሪቱ ከቤልጅየም ቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችው በዛሬዋ እለት በ1952 ነበር። የዕለቱን ከታሪክ ዝግጅታችን ትኩረቱን ከዚህ ላይ አድርጓል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተብላ የምትጠራዋ የመካከላኛው አፍሪካ ሀገር የተፈጥሮ ሃብትን የታደለች በቆዳ ስፋቷም ቢሆን ከአፍሪካ የሁለተኝነት ቦታውን የያዘች ናት። የምዕራባውያኑ እግር ኮንጎን መርገጥ ከጀመረ የሰነባበተ ቢሆንም የቤልጅየም ምክር ቤት በ1901 ዓ.ም. በማዕድን ሀብቷ የበለጸገችውን ኮንጎን በቅኝ ግዛትነት ጠቅልሏል።

የቤልጅየም ቅኝ ግዛት ጉዳዮች ሚኒስተር አስፈጻሚ አካል በቅኝ ግዛት ምክር ቤት እገዛ ወደ ኮንጎ ተላከ። የቤልጅየም ኮንጎ ላይ የቤልጅየም መንግስት የህግ አውጭ ስልጣንን መያዝ ጀመረ።

የቤልጅየም ኮንጎን የቅኝ ግዛት ነገር ልዩ የሚያደርገው በሁለቱም የአለም ጦርነቶች ቀጥታ ተሳትፎ ማድረጉ ነው።

በመጀመሪያው የአለም ጦርነት እ.ኤ.አ. በ1916 እና 1917 በምስራቅ አፍሪካ ዘመቻ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራት። እንግሊዝ፣ ጀርመን እና ፖርቹጋል በትብብር የጀርመን ምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት ላይ ወረራ ፈጽመው ነበር።

በአንደኛው የአለም ጦርነት ቤልጅየም ኮንጎን በመጠቀም በምስራቅ አፍሪካው ዘመቻ ላደረገችው አስተዋጽኦ ተሸልማበታለች።በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ቢሆን ኮንጎ ለቤልጅየም ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነበረች። የቤልጅየም ኮንጎ ኃይሎች በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ተሳትፈዋል።

በጣሊያን የቅኝ ግዛት ኃይልን በሃገራችን ኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ክፍል በመዋጋትም ተሳትፈዋል።

በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች በቤልጅየም ስር በነበረችው ኮንጎ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ጨመሩ። በ1952 ዓ.ም. ቤልጅየም ማሻሻያዎችን ከማድረጓ ዘጠኝ ቀናት አስቀድሞ በኮንጎ ሊዮፖልድቪል አመጽ ተቀሰቀሰ። አማጺዎቹ ንብረት ዘረፉ፤ አቃጠሉ፤ ቤልጂየማውያንን አጠቁ። በረብሻው 49 የኮንጎ ሰዎች ሲገደሉ 249 ያክል ቆስለዋል።

የጊዜው አስተዳደር ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ ብሎም የኮንጎ ተወላጆች ይበልጥ በምክር ቤቶች እንዲካተቱ እንደሚያደርግ ቃል ለመግባት ተገደደ። በዚያው አመት 120 የሚደርሱ ፓርቲዎች በምርጫ ለመሳተፍ ቀረቡ። ከእነዚህ ፓርቲዎች አንዱ የኮንጎ ብሄርተኝነትን የሚያቀነቅነው ፓትሪስ ሉሙምባ ያሉበት የኮንጎ ብሄራዊ እንቅስቃሴ ፓርቲ ነበር። የታሰበው ምርጫ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተከለከለ።

የቤልጅየም መንግስት ከ13 የኮንጎ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ 96 ተወካዮች ጋር ለድርድር ተቀመጠ። ቤልጅየም የኮንጎን ነጻነት ለማክበር ተስማማች። ከስምምነቱ ሶስት ቀናት በኋላ በዛሬዋ እለት ከ62 አመታት በፊት አፍሪካዊቷ ሀገር ኮንጎ ነጻነቷን አገኘች።

የኮንጎ ብሄራዊ እንቅስቃሴ (Mouvement National Congolais) ፓርቲ በአብላጫ ድምጽ አሸነፈ። ፓርቲው ከሌሎች 12 ፓርቲዎች ጋር ደካማ ጥምረት የመሰረተ ሲሆን የ35 አመቱ ፓትሪስ ሉሙምባ የሀገሪቱ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኑ።

በነጻነት ክብረ በዓሉ ቀን የቤልጅየሙ ንጉስ ቦዱዊን የቤልጅየም ቅኝ ገዥዎችን በተለይም ሊዮፖልድ ሁለተኛን የሚያወድስ ንግግርን አደረጉ። ፓትሪስ ሉሙምባ በምላሹ የኮንጎ ዜጎች በቤልጅየም ቅኝ ግዛት ስር የደረሰባቸውን ውርደት የሚገልጽ ብሄራዊ ንግግር አደረጉ።

ኮንጎ ነጻነቷን ካገኘች ከሳምንት በኋላ ፓትሪስ ሉሙምባ በኮንጎ ሰራዊት ውስጥ የነበሩትን የቤልጅየም አመራሮች አሰናብተው በኮንጎሌዝ መሪዎች ተክተዋል።

ግና ኮንጎን ከቤልጅየም ስልጣን የማላቀቅ ስራ ላይ የተጠመዱት ፓትሪስ ሉሙምባ ስልጣን ላይ በወጡ በሰባት ወራቸው በጊዜው በነበረው ፖለቲካዊ ውጥረት በቤልጅየም እና አሜሪካ በተደገፈ መፈንቅለ መንግስት እንዲገደሉ ተደርገዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-06-30