ሀገሬ ቲቪ

እለቱን ከታሪክ - የሆንግ ኮንግ ለቻይና መመለስ

ሆንግ ኮንግ ቻይና በምዕራባውያኑ አብዝታ የምትወቀስበት ክፍል ነች። ይህችው በቻይና ስር ብትሆንም የራሷ አስተዳደር ያላት ግዛት ከእንግሊዝ ለቻይና የተመለሰችው በ1889 ዓ.ም. በዛሬዋ እለት ነበር። በሆንግ ኮንግ በቻይና መንግስት ላይ ተቃውሞዎች እስካሁንም እንዳሉ ናቸው።

በ19ነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቻይና ከአውሮፓ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት አዲስ መጠጥን ሻይን አስተዋውቃለች። በሻይ ምትክ ከብር ማዕድን ውጭ ቻይና ከአውሮፓውያኑ የምትቀበለው አልነበረም። መርከቦች ይመጣሉ፤ ከቻይና ሻይ፣ ሃር እና ቅመማ ቅመም ይወስዳሉ። ቻይናዊያን ግን አንዳች ነገር ከአውሮፓውያኑ አይገዟቸውም። በመጨረሻም ቻይናዎች የሚገዙት አንድ ነገር ተገኘ። የኦፕየም እጽ።

የኦፕየም ንግድን የቻይና ቺንግ ስርዎ መንግስት መቃወሙ ታዲያ የመጀመሪያው የኦፕየም ጦርነትን አስከተለ። እ.ኤ.አ. በ1839 ብሪቴይን የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎቹን ወክላ ቻይናን ወረረች። የእንግሊዝ ጦር የበላይነት በቀጠናው የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች በነጻነት እንዲነግዱ ሁኔታዎችን ቀላል ያደረገላቸው ሲሆን እንግሊዝ በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ብዙም ህዝብ የማይኖርባትን በደቡብ ምስራቅ ቻይና ዳርቻ የምትገኘዋን ሆንግ ኮንግን ለመያዝ አልማ ነበር።

እ.ኤ.አ. በ1842 የመጀመሪያው የኦፕየም ጦርነት ሲጠናቀቅ በናንኪንግ ስምምነት ቻይና ሆንግ ኮንግን ለብሪቴይን ለመስጠት ተስማማች።

የእንግሊዝ ሰዎች የቻይና ዳርቻ ሆንግ ኮንግን ለንግድ ምቹ ቦታ አደረጓት። ግና የቅኝ ግዛት መስፋፋት ፍላጎታቸው በሆንግ ኮንግ የረጋ አልሆነም። በዚህም ሁለተኛው የኦፕየም ጦርነት ተጀመረ። በዚህኛውም ጦርነት እንግሊዝ የሆንግ ኮንግን ግዛት አሰፋች። የእንግሊዝ አዲስ ቅኝ ግዛት የምስራቅ ምዕራብ ንግድ ማዕከል ብሎም የደቡባዊ ቻይና የንግድ በር እና ማከፋፈያ በመሆን እድገት አሳይቷል። ኋላም በአውሮፓውያኑ 1898 ብሪቴይን በፔኪንግ ስምምነት ሆንግ ኮንኝ ለ99 አመታት የመግዛት ስልጣን አግኝታለች። በአመታት ድርድር በ1889 ዓ.ም. ሆንግ ኮንግ ለቻይና እንድትመለስ ሀገራቱ ተስማምተዋል።

ከ150 አመታት በላይ በእንግሊዝ ስር የቆየችው ሆንግ ኮንግ በ1889 ዓ.ም. በዛሬዋ እለት ለቻይና እንድትመለስ ተደረገ። ጥቂት ሺዎች የኮንግ ኮንግ ሰዎች ለቻይና መመለሳቸውን ቢቃወሙም የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስተር ቶኒ ብሌር፣ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዥያንግ ዠሚን እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ማዴላይን አልብራይት በተገኙበት ለቻይና የመመለሷ ነገር በድምቀት ተከበረ።

ሆንግ ኮንግ በሰላማዊ ስምምነት ወደ ቻይና እንድትቀላቀል ከተደረገ በኋላ የሆንግ ኮንግ መሪ ቱንግ ቺ ኋ በአንድ ሀገር ሁለት ስርዓት መርህ ፖሊሲ ቀርጹ። የኮሚዩኒዝም ስርዓትን የምትከተለው ቻይና በብሬቴይን ስር የነበረችውን ሆንግ ኮንግን የካፒታሊዝም ስርዓት ለማክበር ተስማማታለች። በዚህም ሆንግ ኮንግ በኤስያ የካፒታሊስት ማዕከል ሆና የመቆየት ሚናዋን ማስቀጠል ተችሏል።

በየጊዜው የቻይና አስተዳደር በሆንግ ኮንግ ውስጣዊ አስተዳደር ላይ ጣልቃ ይገባል የሚሉ ተቃውሞዎች ይነሳሉ። ከ25 አመታት በፊት ወደ ቻይና በተመለሰችው በሆንግ ኮንግ ግዛት በቻይና መንግስት ላይ ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-07-01