ሀገሬ ቲቪ

“የምክር ቤት አባላት ስልጣናቸውን ሊጠቀሙበት ይገባል።” ዶ/ር ኃይለ ኢየሱስ ታዬ

የአለም ህዝብ ውሳኔዎችን ለመስማት የተወካዮቹን የምክር ቤቶች ድምጽን የመስማት ስርዓት ከገነባ ሰነባብቷል። የፖለቲካ ድርጂቶች እና ራሱ ዲሞክራሲ ላይ እምነት እያጣ ላለው የአለም ህዝብ የጠንካራ ምክር ቤቶች መኖር አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም። ከፖለቲካ ድርጂቶች ተጽዕኖ የተላቀቁ ጠንካራ ምክር ቤቶች የዴሞክራሲ መሰረት ድንጋይ ናቸውም ይባልላቸዋል።

የአለም የፓርላሜንታሪዝም ወይንም የምክር ቤታዊነት ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ በያመቱ ሰኔ 23 እንዲከበር በ1981 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወስኗል። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከ1923 ዓ.ም. ጀምሮ የምክር ቤት ስርዓትን ስታካሂድ ቆይታለች። ከሀገሬ ቴ.ቪ. ጋር ቆይታ ያደረጉት የህገ መንግስት እና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ኃይለ ኢየሱስ ታዬ ስለ ጉዳዩ ይህንን ብለውናል።

“የፓርልያሜንታሪ(ምክር ቤት) ስርዓት የወካይ እና ተወካይ ስርዓት ነው፤ ባለቤቱ ህዝብ ነው ተወካዩ ምክር ቤቱ ነው። ተወካዩ አካል ህዝብን የመወከል፣ ህግ የማውጣት እና አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሚና ይኖረዋል።”

የምክር ቤት ስርዓት ተግባራዊ ሲሆን የፓርቲ ስርአትም ያስፈልጋል ብለውናል። የፓርቲዎች አስፈላጊነት በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሀሳቦችን ወክለው በመፎካከር ካሸነፉ ይዘውት የተነሱትን ሃሳብ ለመፈጸም ነው ብለውናል።

“የፓርላማ ስርዓት ሲከናወን ሁሉም ሰው መወዳደር ስለማይችል በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ሃሳቦች የሚወክሉ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ።”

የሀገራችን የምክር ቤት ስርዓት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የጀመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በውክልና ደረጃ መሻሻል ቢኖርም የምርጫ ሂደት እና የአንድ ፓርቲ የበላይነት ተጽዕኖዎች እንዳሉበት ጠቁመውናል።

“በፓርልያሜንታሪ ስርዓት አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ መንግስት ይመሰርታል። አስፈጻሚው የሚወጣው ከፓርላማው ነው። የስልጣን ክፍፍሉ ግልጽ አይደለም። ስለዚህ ቁጥጥር እና ክትትሉ ደካማ ይሆናል።”

የሀገራችን የምክር ቤት ስርዓት የቁጥጥር እና ክትትል መላላት ፈተናው እንደሆነም ገልጸውልናል። አሁንም ቢሆን ያው ፈተና አብሮት እንደዘለቀም ነግረውናል።

“በኢህአዴግ ጊዜ የነበረው አንድ አውራ ፓርቲ ስለነበር ቁጥጥር እና ክትትሉ ጠንካራ ነበር ማለት አይቻልም። አሁንም ቢሆን ለውጥ የለም ባይባልም ይህን ያህል ጠንካራ የሚባል ለውጥ የለም።”

በምክር ቤት ስርዓት አስፈጻሚ የሆነው አካል ላይ የቁጥጥር እና ክትትል መላላቱን ለማስወገድ ጠንካራ የምክር ቤት ስርዓት ለመገንባት መፍትሄ ያሉትን ዶ/ር ኃ/ኢየሱስ ነግረውናል።

ዶ/ር ኃይለ ኢየሱስ የምክር ቤት አባላት በአስፈጻሚው አካል ላይ የበላይ ስልጣን እንዳላቸው አውቀው የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሰጣቸውን ስልጣን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ጠቁመውናል።

ለሀገር ሲባልም የምክር ቤት አባላት አስፈጻሚው አካልን እስከመቃወም የሚደርስ ስልጣን እንዳላቸው አውቀው አስፈላጊ ከሆነ እስከመቃወም ሊደርሱ ይገባል ብለውናል።

አክለውም የአንድ የፓርቲ የበላይነት በምክር ቤት ውስጥ እንዳይኖር የተቃዋሚዎችን የወንበር ቁጥር ከፍ ማድረግ ለህዝብ የሚቆሙ ተወካዮችን ወደፊት እንዲመጡ ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምክር ቤት አባላት የሀገሪቱ የበላይ ባለ ስልጣን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደመሆኑ ለሀገር ጥቅም ሲባል ስልጣናቸውን ሊጠቀሙበት ይገባልም ብለዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-07-01