ከ1980ዎቹ ጀምሮ ብሄራዊ እና አህጉራዊ የብቃት ማረጋገጫ ማእቀፎች (qualification frameworks) በተለያዩ ምክንያቶች በአለማችን የተለመዱ አሰራሮች ሆነው ይታያሉ፡፡
ከአይነተኛ ምክንያቶቹ መካከል ወጥ እና የጋራ ብቃት ማረጋገጫ ደረጃን መዘርጋት፣ በትምህርትና ስልጠና አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ትስስር መፍጠር እንዲሁም የትምህርት ስርዓቱ ተጠያቂነት እና ተአማኒነት እንዲኖረው ማስቻል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የብቃት ማረጋገጫ ማእቀፍ ስንል የትምህርት ደረጃን እንደ መስፈርት በመውሰድ የተለያዩ ብቃቶችን እድገትና ምደባ ለማየት የሚያስችል መሳሪያ ማለታችን ነው።
በተለይም “የሀገሪቱን አቻ ግመታ” ን ስንመለከት የዚህ ማዕቀፍ አለመኖር ያመጣችውን ተጸእኖ እንደንረዳ ይረዳናል ። አቻ ግመታ ማለት ከውጭ ሀገር የተገኘ የትምህርት ማስረጃን ሀገር ውስጥ ከሚሰጥ ተመሳሳይ ትምህርት ጋር በንጽጽር በመገምገም ተመጣጣኝ ደረጃ እና ስያሜ ያለው መሆኑን መወሰን ማለት ነው።
በውጪ ሀገር ተምረው የሚመጡ ተማሪዮች በተለየም ይህ ማዕቀፍ አለመኖር እየጎዳቸው ነው። ዳዊት ሙሉጌታ የተባለው ወጣት በሳይፕረስ የመጀመሪያ ዲግሪዉን በመከታተል ላይ እያለ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ትምህርቱን አቋርጧል። ወደ ሀገሩ መቶ ትምህርቱን ለመቀጠል ቢፈልግም ይህ ማዕቀፍ ባለመኖሩ እየተጉላላሁ ነው ብሎናል ።
ተማሪ ዳዊትን ጨምሮ ሌሎችንም ተማሪዎች የምናስተናግደው ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ነው እንጂ ያቋረጡ ተማሪዎችን አገልግሎት የምንሰጥበት አግባብ የለንም ሲሉ አቶ ብርሃነመስቀል መላክ በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የአቻ ግመታና የት/ት ማስረጃ ማረጋገጫ ባለሙያ ነግረውናል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ እንግዳ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ቀጣሪዎችም ይቸገራሉ ብለውናል።
ዶ/ር ደረጀ ሀገራዊ የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ሲጽደቅ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣንም ሆነ ተግልጋዮች የሚያገኙትን ጠቀሜታ አስረድተውናል።
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ በበኩላቸው ማዕቀፉ ባለመኖሩ ተቋማቸው በግምት እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ሰነዱን የማጽደቅ ስልጣን በተሰጣቸው ሌሎች ከፍተኛ ሃላፊነት ባላቸው አካላት ይህን ማዕቀፍ ማጸድቅ እንደሚገባ ነግረውናል።
በመቅደስ እንዳለ
2022-07-05
