በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በሚገኘው የቁም ሸማ ገበያ ይገለገሉ የነበሩ ሸማኔዎች በቦታው እንዳይገለገሉ መደረጋቸውን ለሀገሬ ቴ.ቪ. ገልጸዋል። እኛም ከ2012 ዓ.ም. ጀመሮ ከቦታው እንዳይገለገሉ መደረጋቸውን የሰማን ሲሆን ስለ ገበያ ስፍራው የሚመለከታቸውን የአስተዳደር አካላት አናግረናል።
በአዲስ አበባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የሚገኘውን የሽሮ ሜዳ የቁም ሸማ ገበያን ለምርቶቻቸው መሸጫነት ለረዥም ጊዜያት ሲገለገሉበት የቆዩ ቢሆንም አሁን ላይ በገበያ ስፍራው እንዳይገለገሉበት መደረጋቸው ችግር እንዳስከተለባቸው ብሎም ከደንብ አስከባሪዎች ጋር እያጋጫቸው እንደሆነ ለሀገሬ ቴ.ቪ. ገልጸዋል።
የሽሮሜዳ የቁም ሸማ ገበያ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ጎሳዬ ጎቴ ከ1994 ጀምሮ ከመንግስት ካርታ ተሰቷቸው ለአመታት ሲገለገሉበት ከቆዩበት የገበያ ስፍራ የኮቪድ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በቦታው እንዳይገለገሉ ከተደረጉ በኋላ ወደ ቦታው እስከዛሬም እንዳልተመለሱ ገልጸውልናል።
ቀድሞ ሲገበያዩበት ከነበረው የሽሮሜዳ ቁም ሸማ ገበያ ተለዋጭ ቦታ የተሰጣቸው ቢሆንም ወደ ቦታችን እንመለስ የሚል ጥያቄን ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ቅሬታ ሰሚ ጭምር አቅርበው ወደ ቦታቸው ይመለሱ የሚል ውሳኔን ስለማግኘታቸውም አቶ ጎሳዬ ነግረውናል።
ከቅሬታ ሰሚ የተሰጣቸውን ጽሁፍ ይዘው ስፍራው ወዳለበት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ቢመጡም የመገበያያ ቦታው እንዳልተመለሰላቸው ነግረውናል።
“የተሰጠንን ምላሽ ይዘን ስንሄድ ለሌሎች ተሰጥቷል።”
እኛም ይሄንን ጉዳይ ይዘን የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 አስተዳደርን ጠይቀናል።
የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለማየሁ ዱሬ የቁም ገበያውን ለሸማኔዎቹ ለመመለስ በቦታው ላይ ኢ መደበኛ ያሏቸው ሰዎች ንግድ መጀመራቸው እክል እንደሆነ ነግረውናል።
የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጉዳዩ የተፈጸመው በቀድሞ ስራ አስፈጻሚ ነው ያሉን ሲሆን አስተዳደራዊ ምላሽ ለመስጠት አሁን ላይ ቦታው ላይ ያሉት ሰዎች የፍርድ ቤት እግድ ማምጣታቸው ምክንያት እንደሆነም ነግረውናል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የፍርድ ቤት ውሳኔውን ተከትለው የአስተዳደር ምላሽ እንደሚሰጡም ጠቁመውናል።
በአብርሃም በለጠ
2022-07-05
