በ1988 ዓ.ም. የመጀመሪያዋ አጥቢ እንስሳ ዶሊ የተሰኘችው በግ በሰው ሰራሽ መንገድ በልጽጋለች።
የዚህችው በግ የተሳካ የማበልጸግ ሙከራ ክርክሮችን እና አድናቆቶችን አስከትሏል።
ይህችው በግ በህይወት መቆየት የቻለችው ለ6 አመታት ቢሆንም የመሰል ምርምር እመርታ ተደርጋ ትወሰዳለች።
ዛሬ ወደኋላ መለስ ብለን አንድ የሳይንስ ሁነትን እንመለከታለን። በርግጥ ጊዜው 1988 ዓ.ም. ነው። ነገሩ የሆነው በዛሬዋ ዕለት ከ26 አመታት በፊት ነው። በሰው ሰራሽ መንገድ አንዲት በግ ከአጥቢ ሴል ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትበለጽግ ተደረገ።
ዶሊ የተሰኘችው ይህችው በግ በስኮትላንድ ሮዝሊን ኢንስቲትውት ነበር የበለጸገችው። ዶሊ አጥቢ እንስሳትን በማበልጸግ ረገድ ቀዳሚዋ ነች።
ይህችው መጀመሪያ ላይ 6LL3 የሚል ስያሜ የተሰጣት በግ በምርምር ከጎለመሰ ህዋስ እንድትወለድ ተደረጓል። ዶሊ የሚለውን ስያሜዋንም ከድምጻዊዋ ዶሊ ፓትሮን አግኝታለች።
የዶሊ ከሩብ ክፍለ ዘመን በፊት በዛሬዋ እለት መወለድ ከሴል አጥቢ እንስሳን የማበልጸግ ሙከራዎች ስኬት ነው። ይህችንው በግ የማስገኘት ሙከራ ባለቤትነትን በስኮትላንድ ሮስሊን ኢንስቲትውት የጽንስ ሀኪሞች የሆኑትን ካረን ዎከርን እና ቢል ሪቼን ያካተተው ቡድን ይወስዳል።
ካረን ዎከር እና ቢል ሪቼ በሙከራ ቱቦ የበለጸገችው በግ ዶሊ እናት እና አባት ተብለውም ይታወቃሉ።
ከዶሊ መገኘት አስቀድሞ ከ250 በላይ መሰል ያልተሳኩ የሙከራ ምርምሮች ተደርገዋል።
የምርምር ዘርፉ የወቅቱ መነጋገሪያ የሆነችው ዶሊ ለህዝብ ይፋ ስትሆን አድናቆትና ድንጋጤ ታክለው የክርክር ምንጭ አድርገዋታል። ክሎኒንግ ተብሎ የሚጠራው የዚህ ምርምር ዘርፍ ደጋፊዎች የዶሊ ግኝት ለህክምናው ዘርፍ ትልቅ እመርታ ሊያመጣ እንደሚችል፣ በምርምር እንዲሻሻሉ የሚደረጉ እንስሳት ለሰው የአካል ክፍልን መለገስ እንዲችሉ ብሎም እንደአልዛይመር ላሉ የነርቭ በሽታዎች ህዋሶችን ለማበልጸግ የሚያስችል የምርምር ጅማሮ አድርገው ገልጸውታል። ጥቂት ተመራማሪዎችም በመጥፋት ላይ ያሉ እንስሳትን ለመታደግ እንደሚያስችል ጠቁመው ነበር።
በሌላ በኩል ድርጊቱን የሚነቅፉት የክሎኒንግ ቴክኖሎጂ ስነ ምግባር የጎደለው እና አደገኛ አድርገው ተመልክተውታል። በተለይም አጥቢ እንስሳን ከማበልጸግ በኋላስ ሰውን ወደ ማበልጸግ ቢታለፍስ ሲሉ የድርጊቱን ስነ ምግባር አልባነት ለማሳየት ሞክረዋል።
በላብራቶሪ እገዛ እንድትበለጽግ የተደረገችው በግ ዶሊ በህይወት ዘመኗ ዴቪድ ከተሰኘ አውራ በግ ጋር ተቆራኝታ አራት ግልገሎችን መውለድ ችላለች። ኋላም በ1994 ዓ.ም. በአርትሪትስ እና የሳንባ በሽታዎች መጠቃት ጀመረች። ህክምናዋም የማበልጸግ ሂደቱ በዘር የሚተላለፍ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ጥያቄ አንስቷል።
ቀጣይነት ባለው የሳንባ ህመም ከታመመች በኋላ በዚያው አመት በ6 አመቷ ሞታለች።
ከሞተች በኋላ የሮዝሊን ኢንስቲትውት የዶሊን ሙት አካል በኤደንበርግ ለሚገኘው የስኮትላንድ ብሄራዊ መዘክር አስረክቧል። የዶሊ አካል ለብሄራዊ መዘክሩ በትልቁ ከሚጎበኙ ንብረቶች አንዱ ሆኗል።
በአብርሃም በለጠ
2022-07-05
