ለዓለም የሸቀጦች ዋጋ መናር እና ለአለም የምግብ ቀውስ ሌሎች ገፊ ምክኛቶች ቢጠቀሱም ቻይና እና አሜሪካ የገቡበት የንግድ ጦርነት ግን ነገሩን የበለጠ አወሳስቦታል እየተባለ ይገኛል።
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሰሞኑ በቪዲዮ ውይይት አድርገው ነበር።
ወዲህ ከምዕራቡ ዓለም፣ ያለችው የሚሆንላት፤ የልቧን መሻት ካለ ማንም ከልካይ የምትፈጽም ሀገር።
ወዲያ ከምስራቁ ደግሞ በቅርብ ጊዚያት ውስጥ የዓለምን የኢኮኖሚ መዘውር በእጇ ያደረገች የማኦ ዜዱንግ ሀገር።
የዚህ ዘመን ልዕለ ኃያላን ሀገራት፤ አሜሪካ እና ቻይና።
ወትሮም ቢሆን የሚበልጣትን የማትሻዋ ሀገር ከቀሪው ዓለም ተርፎ በራሷ ላይ የመጣባትን የቻይናን የኢኮኖሚ ተፅዕኖ እንዴት ከላይዋ እንደምትራግፍ መላው ጠፍቶባታል።
ከሰሞኑ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሀገራቸው ሆነው በቪዲዮ መክረዋል።
አሜሪካ በግምጃ ቤት ፀሐፊዋ ጃኔት ዬለን በቻይና በኩል ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚንስተሯ ሊ ዩ ሄ ነበር የተወከሉት።
በውይይታቸውም ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ተነስተዋል። በዋናነትም የሸቀጦች ዋጋ መናር እና የምግብ ዋስትና ሁነኛ አጀንዳዎች ነበሩ ነው የተባለው።
ሀገራቱ የገቡበትን የንግድ ጦርነት የአሜሪካ የግምጃ ቤት ፀሐፊዋ፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የንግድ ስርዓት ሲሉ ቻይና እና አሜሪካ ያላቸውን የንግድ ሁኔታ ገልፀውታል።
በርግጥ ይላሉ የአውስትራሊያ ቻይና ግንኙነት ኢንስቲቲውት ዳይሬክተር ጄምስ ላውረንሰን ከአልጄዚራ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “የዬለን ንግግር ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ባለስልጣናት ከተናገሩት ይለያል የሚባል አይደለም። ጉዳዩ አሜሪካ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን ቻይና ላይ ከመሰንዘር የተሻገረ ምን ልታደርግ አስባ ይሆን የሚል ነው”
ወደ ኢኮኖሚ ጦርነት የተሻገረው የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ጉዳይ ለሸቀጦች ዋጋ መናር፤ ለምግብ ዋስትና ቀውስ ዋነኛ ምክንያት ስለመሆኑ ሁለቱም ሀገራት ያምናሉ።
ነገሩ ከ2008 ዓ.ም ይጀምራል።
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ሲጀምሩ ካነሷቸው ሀሳቦች ውስጥ ዋነኛው የቻይና እና የአሜሪካ የንግድ ልውውጥ ነው።
በጊዜው ትራምፕ ቻይናን የአሜሪካ የሆኑ የአዕምሮ ንብረቶችን እየሰረቀች ለራሷ ተጠቅማበታለች ሲሉም ወንጅለዋት ነበር።
ከትራምፕ ወደሥልጣን መምጣት በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ልዩነት የበለጠ ወደመሻከሩ አጋደለ።
በወርሃ ሰኔ 2010 ዓ.ም አንስቶ እስከ ሐምሌ 2011 ዓ.ም ድረስ ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ ከ550 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቀረጥ ጥለዋል።
ቻይናም ብትሆን የአፀፋ እርምጃ በመውስድ ከ185 ቢሊዮን ዶላር በላይ ቀረጥን በአሜሪካ ምርቶች ላይ ጣለች።
በ2012 ዓ.ም በአሜሪካ እና በቻይና መካከል የተደረገው የንግድ ልውውጥን ብንመለከት እንኳ 615.2 ቢሊዮን ዶላር ሆኖ ተመዝግቦ ይገኛል።
ከዚህም ውስጥ አሜሪካ ወደ ቻይና የምትልካቸው እቃዎች እና አገልግሎቶች ተደምረው 164.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሲያስገኙ አሜሪካ ከቻይና በምታስገባቸው ሸቀጦች እና አገልግሎቶች 450.4 ቢሊዮን ዶላር ከካዝናዋ እንድታወጣ አድርጓታል።
ይህ ነው እንግዲህ የአሜሪካ ባለስልጣናትን ፍትሀዊ የንግድ ሥራዓት ውስጥ እንዳልሆኑ እንዲሰማቸው ያደረገው።
ነገሩ ቻይና ወደ አሜሪካ በምታስገባቸው ምርቶች ሳቢያ የመጣ አይደለም ይላሉ በካርኔጊ እስያ ፕሮግራም ውስጥ ከፍተኛ ባልደረባ የሆኑት ዩኮን ሁዋንግ ።
እኚህ ሰው እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ትራምፕ ማእቀቦችን መጣል ከጀመሩ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ብናይ ቻይና ቁጥር አንድ የአሜሪካ የንግድ አጋር ነች። የንግድ ግንኙነታቸውም ከዚህ ቀደም ከነበረው በከፍተኛ ሁኔታ እድገትን እያስመዘገበ ይገኛል።
ትራምፕ እንደሚሉት የቻይና ኩባንያዎች በአሜሪካ ውስጥ ገብተው በስፋት ኢንቨስት ማድረጋቸው የአሜሪካን አቻዎቻቸውን እየጎዳ ከሆነ፤ ለምን አሜሪካስ በቻይና ኢንቨስት አታደርግም ሲሉም ይሞግታሉ።
ከሰሞኑ በነበረው የሁለቱ ሀገራት የከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ምክክር ታዲያ ዓለም የተደቀነባትን የሸቀጦች ዋጋ መናር እንዴት እንፍታው ለሚለው የተወሰነም ቢሆን ለመስማማት የቀረቡ ሀሳቦች የተነሱበት ነበር።
ቻይናም ይህንኑ ሁኔታ በጥልቀት እንደምትመለከተው የተናገሩት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ቀጣይነት ያላቸው ስራዎች እንደሚጠበቁም አልሸሸጉም።
ለአብነትም አሜሪካ በቻይና ላይ የጣለቻቸው ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ የቀረጥ እና ሌሎች ማዕቀቦች በመፍሔው ላይ ጥላ እንዳያጠሉ ሊታሰብባቸው እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በቅርቡ በቻይና ላይ የተጣለውን ከፍተኛ ቀረጥ ለማቅለል ሀሳብ እንዳላቸው ማንሳታቸው አይዘነጋም።
ይህም ከቁጥጥር እየወጣ ያለውን የዓለምን የሸቀጦች ዋጋ እና የምግብ ፍላጎትን ለማስተካከል መልካም ጅምር ነው እየተባለለትም ይገኛል።
የሁለቱ ሀገራት ምክክርም በአለም ምጣኔ ሀብት ላይ የተሻለ ለውጥን ለማምጣት ተስፋ የሚጣልበት ሊሆን ይችል ይሆናል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-07-05
