መቼም ሀገሬው አማኝ ነው። አማኝ በሆነ ማህበረሰቡ ውስጥ ደግሞ ሀይማኖቱ የሚያዛቸውን ተግባራት መፈፀም ውዴታም ግዴታም ነው።
ከእነዚህ የሀይማኖት መርሆች አንዱ ካለን ላይ ቀንሰን፣ ሰፍረን ለሀይማኖት ተቋማት መባ አልያም አስራት እናገባለን። ይህ በየትናውም ሀይማኖት ውስጥ ያለ ስርዓት ነው።
ዛሬ ደግሞ ወደ ሀይማኖቱ ጎራ ይዘናችሁ እንዘልቃለን ። በሩሲያ ባለቤቴ ለቤተክርስቲያን በምትሰጠዉ ገንዘብ ተማርሬያለሁ ያለ ግለሰብ አለምን በእጅጉ ያስቆጣ አንድ ተግባር ፈጸመ ። ባለቤቴ ገንዘባችንን ለቤተክርስቲያን ትሰጣለች በሚል በመኪናው ውስጥ ቤንዚን በጣሳ በመያዝ ቤተክርስቲያኗን በእሳት አቃጠለ ።
ነገሩ የተከሰተው ባሳለፍነው ሳምንት በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ አውራጃ በፓርጎሎቮ መንደር ውስጥ ነው ። የ አካባቢው ሰው የ አምልኮ ስነ ስራዐት የሚያደርጉበት የቅዱስ ባሲል ቤተክርስቲያን አለ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ለእምነት ተቋሞቻችን ካገኘናት ላይ ቀንሰን እንደምንሰጠው ሁሉ በሩሲያ የቅዱስ ባሲል ቤተክርስቲያን አገልጋዮችም ካገኙት ቀንሰው ለ ቤተክርስቲያናቸው የመስጠት ፈጣሪያቸውን የማመስገን ልምድ አላቸው ።
የዚህ ግለሰብ ሚስትም ልክ እንደ አካባቢው ነዋሪ ሁሉ ለቤተክርስቲያንዋ ያላትን የመስጠት በጎ ልምድ አላት ። ታዲያ ይህ የሚስትየዋ ድርጊት የሚያበሳጨው ባል ተይ ይሄን ነገር አቁሚ ማለት ከጀመረ ሰነባብትዋል አልፎ አልፎም እጁን ያሳርፍባት ነበር ።
ነገር ግን የባለቤትዋ ቁጣም ሆነ ዱላ ያልበገራት እንስት እንደወትሮው ሁሉ ለ ቤተክርስቲያን የምትሰጠውን ገንዘብ አጠናክራ ቀጠለች ። ይሄኔ ነበር የሚስት በጎ ምግባር ንዴቱን ያባባሰው ባል በቤተክርስቲያኗ ላይ እሳት የለኮሰው።
በወቅቱ በ አካባቢው የነበሩ ሰዎች እሳቱን ለማጥፋት ባደረጉት ርብርብ አደጋውን ለመቀስ ቢቻልም በአካባቢው የሚገኙ የዜና ማሰራጫዎች እንደዘገቡት ግን ግለሰቡ የለኮሰው እሳት በፍጥነት በመስፋፋቱ የእንጨት ጣሪያውን እና የህንፃው ግድግዳ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ።
የአካባቢው ነዋሪዎችም የአምልኮ ቦታዉ በእሳት ሲቃጠል በእንባ ተሞልተዉ ታይተዋል፡፡ እሳቱን ለማጥፋት የመጡት ሰዎች መጀመሪያ እሳቱን ስንመለከት በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የተነሳ መስሎን ነበር ።
በቦታው ስንደርስ ግን ያየነው ልባችንን ሰብሮናል ሲሉ ለሀገሬው ቴሌቭዥን ተናግረዋል ። የ36 ዓመቱ የአካባቢው ነዋሪ ከባለቤቱ ጋር በገንዘብ ተጣልቶ ቤተክርስቲያኑን ለመበቀል መወሰኑም ብዙዎችን አሳዝኗል አስቆጥቷልም ።
ግለሰቡም በ ፖሊስ ቁጥጥር ላይ ውሎ ፍርዱን እየተጠባበቀ ይገኛል ።
በሳምሶን ገድሉ
2022-07-05
