ሀገሬ ቲቪ

የአማራ ክልል ቱሪዝም መቀዛቀዝ

እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ ልዩ የቱሪዝም መስህብ፣ እልፍ ታሪካዊ መዳረሻዎች፣ ቱባ ባህል እና ውብ መልከዓምድራዊ አቀማመጥ የታደለው የአማራ ክልል ቱሪዝም፡፡ በክልሉ ቱሪዝም ላይ ሕይዎታቸውን የመሰረቱ ዜጎች እና አካባቢዎች ቁጥራቸው ይሄ ነው የሚባል አይደለም፡፡

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስከ ሕግ ማስከበር ዘመቻው የቱሪዝም ዘርፉን ላለፉት ሦስት ዓመታት እየፈተኑት ይገኝል፡፡ በዚህም ክልሉ ከቱሪዝም ዘርፉ ከ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አጥቷል።

“በጣና ሃይቅ አካባቢ በአሳ ማስገርና በጀልባ የትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተዳክሟል ብለዋል’’

ክልሉ ሰላም የለውም በሚል የተዛባ መረጃ እየተዘዋወረ በመሆኑ የቱሪዝሙን ዘርፍ እያቀዛቀዘው ነው ሲሉ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪዎች ዋጋ እየከፈሉ ነው። ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎችም በገንዘብ የማይተመን ቅርሶችን፣ የታሪክ አሻራዎችን ክልሉ እንዳጣ ነግረውናል። ቢሮውም የክልሉን ቱሪዝም ያነቃቃል ያለውን የቱሪዝም ፖሊስ አቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል ሲሉ አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል።

በክልሉ በሰባት ዞኖችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች 91 ቋሚ ቅርሶች ተጎድተዋል፣ 1721 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች መዘርፋቸውን ከቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የተጎዱትን ቅርሶች ለመጠገንም ከ 66 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ክልሉ ያስፈለገዋል፡፡

በመቅደስ እንዳለ
2022-07-06