ሀገሬ ቲቪ

የአብን መግለጫ

በምእራብ እና ምስራቅ ወለጋ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ አየተፈፀመ ያለው ስልታዊ የዘር ማጥፋት ነው ብሎ እንደሚያምን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታወቋል።

ፓርቲው ላለፉት አራት ዓመታት የተፈፀመውንና የቀጠለውን ‘’የዘር ማፅዳት ወንጀል’’ ሲል በስሙ እንዲጠራና እውቅና እንዲያገኝ ጠይቋል።

የዘር ጭፍጨፋ እንዲፈፀም ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ፣ ግለሰቦች፣ እንዲሁም ሚዲያዎች በወንጀሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ አሳስቧል። ጨምሮም የኦነግ እና የኦፌኮ አመራሮች የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ወንጀሉ እንዲፈፀም ሲያነሳሱ ነበር ብሏል።

ለአብነትም ጃዋር መሐመድን ጨምሮ ሌሎች የኦሮሞ ሊሂቃን ነን የሚሉ ግለሰቦች የአማራ ክልል መንግስት ሃይሎች ወደ ኦሮሚያ ገብተዋል የሚል ሀሰተኛ መረጃ ሲያሰራጩ ነበረ ሲል በመግለጫው አስታውቋል።

አብን በዛሬው መግለጫው ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ፣ በወለጋ እና አካባቢው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ እና በፌደራል የፀጥታ ተቋማት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ አሳስቧል።

በተጨማሪም የጥቃቱ ሰለባ እና ተጋላጭ አማራዎች ራሳቸውን ለመከላከል ይረዳቸው ዘንድ በሚሊሻነት ተደራጅተው መሳሪያ እንዲታጠቁ ጠይቋል።

በመቅደስ እንዳለ
2022-07-06