ሀገሬ ቲቪ

የአና ፍራንክ ስደት

ዓለምን በጀርመን እጅ የማስገባት ዕቅድ ይዞ የተነሳው ናዚ አውሮፓን እያመሳት ነው። ሆላንድ በናዚ እጅ ወድቃለች። በዛሬዋ እለት በ1936 በሆላንድ የሚኖሩት አይሁዳውያኑ አና ፍራንክ እና ቤተሰቦቿ ከናዚ የግፍ ጭፍጨፋ ለማምለጥ በአምስተርዳም በአንድ መጋዘን በድብቅ ቦታ ለመሸሸግ ተገደዋል። ከመደበቃቸው አንድ ቀን አስቀድሞ የአና ታላቅ እህት ማርጎ ወደ ናዚ የስራ ካምፕ እንዲጋዙ የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷት ነበር።

ለዓለም ከናዚ የመደበቅ ጉዞዋን እና ሃሳቦቿን በማስተዋሻዋ በማስፈር የደረሰችው በሙሉ ስሟ አኔሊስ ማርዬ ፍራንክ ተብላ የምትጠራው አና ፍራንክ ውልደቷ በጀርመን ፍራንክፈርት በ1921 ዓ.ም. ነው።

አና ገና የአምስት አመት ልጅ ሳለች በጀርመን ጸረ አይሁድ አቋም ያለው የናዚ ፓርቲ ስልጣን ያዘ። በዚህም አና እና ቤተሰቦቿ ወደ አምስተርዳም ለመሰደድ ተገደዱ። በዚያም ጥሩ የሚባል አዲስ ኑሮ ጀምረዋል። አናም ትምህርት ጀምራለች።

የሸሹት ናዚ በ1932 ዓ.ም. ሆላንድን ተቆጣጠረ። ናዚ ጠበቅ ያለ ህግን በአይሁዳውያኑ ላይ አወጣ። የአይሁዳውያኑን የመንቀሳቀስ ሁኔታ የሚገድብ ነው። አይሁዳውያን ከአይሁዳውያን ውጭ የሆኑ የንግድ ቦታዎች በቀር እንዳይሄዱ ተከለከሉ።

ህጻናቱ በአይሁዳውያን ትምህርት ቤት ብቻ ተለይተው እንዲማሩ ተደረገ። ብዙም ሳይቆይ አይሁዶች መታወቂያ ለማግኘት የዳዊት ኮከብን ለመለያ በልብሳቸው ላይ ማድረግ ይጠበቅባቸው ጀመር።

በዚያን ጊዜ የ13 ዓመቷ አና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቿን ከጓደኞቿ እና ቤተሰቦቿ ጋር ያላትን ግንኙነት በዙሪያ እያደገ ስላለው አደገኛ ዓለም ሁኔታ በዕለት ማስታወሻዋ ላይ መመዝገብ ጀምራለች። ደራሲ ወይንም ጋዜጠኛ የመሆን ህልምም ሰንቃ ነበር።

የአና አባት ኦቶ ፍራንክ በናዚ ማጎሪያ ካምፕ እንዳይወሰዱ ስጋት አድሮበታል። ኦቶ የመጽሃፍት ጠባቂውን ሜፕ ጌስን አማከረ። ቤተሰቡን እንድትደብቅለትም ጠየቃት። ሌሎች ተቀጣሪዎቹንም ኦቶ እንዲረዱት ጥያቄ አቀረበ። የኦቶ ቤተሰቦችን ለማገዝ የተስማሙት ሰራተኞች ምግብ ለማቅረብ፣ የውጩን ዜና ለቤተሰቡ ለማቅረብ የራሳቸውን ህይወት አደጋ ላይ ጣሉ። ወደ ሚስጥራዊው የቤተሰቡ መደበቂያ መግቢያ ከመጻህፍቱ መደርደሪያ ጀርባ የተደበቀ ነው።

በቀጣዮቹ ሁለት አመታት በስውሩ መጋዘን መደበቂያ ውስጥ አና ከቤተሰቦቿ ጋር መደበቃቸው የግድ ሆነ። የነበራቸውን ህይወት ግን በዕለት ማስተዋሻዋ ታሰፍራለች።

ግና የመጋዘን ውስጥ የመሸሸግ ህይወት ከሁለት አመታት በኋላ ማብቃቱ የግድ ሆነ። የአና ፍራንክ ቤተሰቦች ያሉበት ሚስጥራዊ መደበቂያ በናዚ ታወቀ። አይሁዳዊ ቤተሰቦቹ የፍራንክ ቤተሰብ እና ሌላ መሸሸጊያ ስፍራውን የተጋራ ቤተሰብ እና አንድ አይሁዳዊ ሰው እነርሱን በመደበቅ ከተባበሩት ሁለት ክርስቲያኖች ጋር በስቃይ ወደ ተሞላው የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ተወሰዱ።

የአናና የቤተሰቧ ብሎም አብረዋቸው የተሸሸጉት ሰዎች የመደበቅ ህይወት በፖላንድ ወደሚገኘው ወደ ኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ በመወሰድ ተጠናቀቀ።

ኋላም የፖላንድ በሶቭየት ነጻ መውጣት እውን እየሆነ ሲመጣ አና ከእህቷ ማርጎ ጋር ወደ ጀርመን የበርገን ቤልሰን ማጎሪያ ካምፕ ተዛወሩ። ሁለቱ እህታማቾች በማጎሪያ ካምፑ ባለው ሁኔታ እየተሰቃዩ ቆይተው ኋላም በታይፈስ ተይዘው አረፉ።

ግና አፍላዋ አና የጻፈችው የዕለት ማስታወሻዋ በ1940 በጀርመን የህትመት ብርሃን አየ። ኋላም ከአምስት አመታት በኋላ ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉሞ ለዓለም አንባቢያን ለንባብ በቃ። ይሄው የአና ማስታወሻ ወደ 70 ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በናዚ የግፍ ጭፍጨፋ ሰለባ ለሆኑ 6 ሚሊዮን አይሁዳውያን በጭፍጨፋው ድምጽዋ ለጠፋው አና ጭምር የስነ ጽሁፍ ምስክር ተደርጎ ያወሰዳል።

ለሁለት አመታት የተሸሸጉባት ቤትም በ1952 ዓ.ም. የአና ፍራንክ ቤት ተብላ ወደ መዘክርነት ተቀይራለች።

በአብርሃም በለጠ
2022-07-06