መቼም ዘመን ደግ ነው መጓጓዣውም ቄንጠኛ እየሆነ፣ መንገዱም እንደየ ሁኔታው እየተለዋወጠ አሁን ላይ ደርሰናል።
ብዙ ዘመናዊና አስደናቂ መንገዶች በዓለማችን ላይ ይገኛሉ።
እያወራን ያለነው ስለ አፓልት መንገዶች መሆኑን ልብ ይለዋል።
አፈር ጠርጎ፣ ጠጥር አልብሶ ሬይንጅ አንጥፎ፣ የሚሰራዉን አስፋልት አብዛኞቻችን በተለያየ አጋጣሚ ተመልክተናል።
ታዲያ ሬንጁ ከሙቀቱ ጋር ተደምሮ ለሠራተኞችም በእዚያ ለሚያልፉም ደስ የማይል ሽታን ለአፍንጫ ያቀብላል።
ከዚህ የተለየ ከመራመድ አልፎ ብሉኝ ብሉኝ የሚል አስፋልት መኖሩን ሰማን እና ልናስተዋውቃችሁ ወደናል።
መቼም ምን አይነት ይሆን ማለትዎ አይቀርም።
ከወደ ራሺያ አስፓልቱ እንጆሪ እንጆሪ ስለማለቱ ሰማን።
በሩሲያ ሌኒግራንድ በተባለ ክልል የተሰራው ይህ የአስፓልት መንገድ ነው እንጆሪ እንጆሪ አለ መባሉን የሰማንለት።
በክልሉ አስፓልት መንገድ በመስራት ላይ የነበረ አንድ ኩባንያ ከትኩሱ ሬንጅ የአስፓልት ንጣፍ የሚወጣው ሽታ ሰራተኞቹን ቢረብሽበት መላን ዘየደላቸው።
የሰራተኞቹን ምቾት ለመጠበቅ ቆርጦ የተነሳው የሩሲያ ኩባንያ ለሙከራ ያህል ወደ 300 ቶን የሚጠጋ የእንጆሪ ጣዕም ያለው ዘይት እና የአስፓልት ድብልቅን አዘጋጀ።
ከዚያም ሙከራውን በሌኒንግራድ ቬሴቮሎቭስክ አውራጃ 700 ሜትር አዲስ አስፓልት በመዘርጋት በስኬት ማጠናቀቁን አስታቋል።
የኢንጆሪው ጠረን ለምን ያህል ጊዜ ቆየ የሚለውን ማወቅ ባይቻልም አዲሱን ሙከራ ያደረገው ኩባንያ ግን የኢንጆሪው ጣዕም የአስፓልቱን ጥራት በፍፁም አያጎድልም እያለ ይገኛል።
ከጥቂት ወራት አስቀድሞ በፖላንድ ተመሳሳይ ሙከራ መደረጉን ሮይተርስ ከሰሞኑ አስነብቦ ነበር።
የፖላንድ የግንባታ ኩባንያ የአበባ መዓዛ ያለው አስፓልት በሙከራ ደረጃ ስለመሥራቱ አስታውቆ ነበር።
ድርጅቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሠራተኞቹ የተሻለ መዓዛን እያሸተቱ መሥራታቸው የተሻለ የሥራ ተነሳሽነት እንደሚፈጥርባቸው ተናግሮም ነበር።
አዲሱ ሬንጅ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አስፈላጊ ዘይቶች ውህድን የያዘ ነው ተብሏል።
ከእነዚህ ዘይቶች ውስጥ አብዛኞቹ የአስፓልቱን ንጣፍ የቀደመ ጠረን የሚያጠፉ ናቸው።
የተቀሩት ደግሞ ለአፓልቱ የተለየ ጠረንን ይጨምሩለታል ነው የተባለው።
ሁለቱም ኩባንያዎች አዲስ ነገርን ለማስተዋወቅ የሚከሩበት መንገድ ሙገሳን አትርፎላቸዋል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-07-06
