ሀገሬ ቲቪ

አንድ ቻይናዊ በፈተና 2 ሚሊዮን ዩዋን አገኘ

መማር ያስከብራል (የበላ እና የተማረ ወድቆ አይወድቅም)፤ በዚህ አባባል የምንስማማም አሻፈረኝ የምንልም አንጠፋም።

ከአኳላው ዘልቆ ቀለምን ለመቅዳት ከተስተማሪ ቤቱ የገባም፤ የኔታ እግር ስር ተቀምጦ ዳዊት የዘለቀውም ከመድረሳው ደርሶ ከአሊፍ ባታ የተዋወቀም ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አለ።

ፈተና!!!

ተማሪ መሆን የሚከብደው እዚህ ጋር ይመስላል። ከቀለም ቤት ዘልቆ ዕውቀትን የቀዳ ማወቅ አለማወቁ የሚመዘነው የሚቀርብለትን ፈተና ጠንቅቆ የመለሰ እንደሆነ ነው።

መቼም ስለፈተና ሲነሳ ሁላችንም ትምህርትን ሀ ብለን ከጀመርንበት አንስቶ አሁን እስካለንበት ሳንፈተን አልደረስንም። ለእርሶ ከፈተናዎች ሁሉ የትኛው ፈተና ከብዶት ነብር? ፈተናውን የተፈተኑበት ግዜስ መቼ ነው?

አስቲ ውስታችሁን በማህበራዊ ገፆቻችን አጋሩን።

እኛ የዓለማችን ከባዱ ፈተና እንጀራ ስለሆነለት አንድ ግለሰብ እናጫውታችኋለን። ቻይኖቹ ከእንዲህ አይነቱ ፈተና ነው አውታኝ የሚባል ይላሉ።

የዓለማችንብ ከባዱ፣ ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እውቀት ፈላጊዎች ይፈተኑታል የጋኦካዎ የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና። ቻይና የተማሩ ዜጎቿ ወደ ዩንቨርሲቲ ይገቡ ዘንድ የምትፈትናቸው ይህ ፈተና በዓለማችን ካሉ የፈተና አይነቶች ከባዱ ነው ይባልለታል።

ታዲያ ይህን ፈተና ተፈትኖ ወደ ዩንቨርሲቲ መግባትም ከግመል የመርፌ ቀዳዳ መሹለክ ጋር በእኩል የሚታይ ነው፤ ለቻይናውያኑ።

ፈተናው በርግጥ ለዩንቨርሲቲ መግቢያነት ብቻም አይደለም የሚያገለግለው። ሰዎች ለስራ ብቁ መሆናቸውንም የሚመዝኑበት ነው።

ታዲያ ይህን ፈተና ደጋግሞ በመውሰድ እና ፈተናውን በሚገባ በማለፍ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ኪሱ ማስገባት የቻለው ቻይናዊ መነጋገሪያ ሆኗል።

ነገሩ ወዲህ ነው፤ በሀገረ ቻይና ያሉ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸው ይህንን ፈተና እንዲያልፉላቸው ለማበረታታት ፈተናውን ላለፈ ገንዘብ ይሸልማሉ።

ታዲያ ጋኦካዎ የውሃ መንገድ የሆነለት ኳን የተባለው ይሄው ቻይናዊ ወጣት ፈተናዎቹን ሦስት ግዜ በመውሰድ እና በማለፍ 2 ሚሊዮን የቻይና ዩዋን ከገንዘብ ቋቱ አስገብቷል።

የቻይናውን ገንዘብ ወደ ብር ስንለውጠው ከ15 ሚሊዮን በር በላይ ማለት ነው። ኳን ታዲያ በ2012፣ 2013 እና 2014 ዓ.ም በሦስት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመማር ፈተናዎቹን ወስዷል።

ከዛም ትምህርት ቤቶቹ ያቀረቡትን የሽልማት ገንዘብ እየተጨበጨበለት ተቀብሏል። ታዲያ የሀገሪቱ መንግስትም በዚህ የተቆጣ ይመስላል።

ኳን እንደተማረባቸው ያሉ ትምህርት ቤቶች የገዛ ስማቸው እንዲገዝፍላቸው በማሰብ ድርጊቱን እንደሚፈፅሙ ተሰምቷል።

አሁን ኳን አገኘ የተባለው ገንዝብ ከዩንቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ጎምቱ ተማሪዎች በ2 ዓመታት ውስጥ እስኳን ማግኘት የሚችሉት አይደለምም ነው የተባለው።

ትምህርት ቤቶቹ እየፈፀሙ ያሉት ተግባር ትውልድን ገዳይ ነው እና ልናስቆማቸው ይገባል ሲሉ የትምህርት ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ኦንግ ቢንቺ ተናግረዋል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-07-07