1982 ዓ.ም. ነው። አንድ የዓለምን ዓይን እና ጆሮ መያዝ የቻለ ሰው በቤቱ የዳንስ ልምምድ በማድረግ ላይ ነው። ዓለም በሙዚቃዎቹ ብሎም በዳንሱ የተደመመለት ይህ ሰው በልምምድ ላይ ሳለ የደረት ህመም አጋጠመው።
ወደ ሆስፒታልም ለመግባት ተገደደ። በዛሬዋ ዕለት ወሬውን የዓለም መገናኛ ብዙሃን ተቀባበሉት። ምክንያቱም ይህ ሰው ማይክል ጃክሰን ነበር።
የ20ኛው ክፍለ ዘመን ስመ ጥሩ ሙዚቀኛ ማይክል ጆሴፍ ጃክሰን ውልደቱ በአሜሪካ ኢንድያና በ1950 ዓ.ም. ነው። ማይክል ጃክሰን የቤተሰቡ ስምንተኛ ልጅ ነው። በ1950ዎቹ አጋማሽ ከታላላቅ ወንድሞቹ ጋር የሙዚቃ ጉዞውን ጀምሯል።
ማይክል ጃክሰንን ጨምሮ አራት ወንድሞቹን ያቀፈው ቡድን ጃክሰን 5 (Jackson 5) የተሰኘ ስያሜን ይዟል። ኋላም ስማቸውን ጃክሰንስ ሲሉ ለውጠውታል።
በጃክሰንስ የተማረከው የሞቶውን ሪከርድስ ፕሬዝዳንት የሆነው ቦሪ ጎርዲ ጁንየር ከቡድኑ ጋር ተፈራርሟል።
ወጣቶቹ ጃክሰኖች ወደ ስኬት መንደርደሩን ተያያዙት።
በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የፖፕ ሙዚቃ ላይ ተቀዳሚ መሆን የቻሉ “I Want You Back” ፣ “ABC” ፣ “The Love You Save” እና “I’ll Be There” የተሰኙ ስራዎችን ለአድማጮች አደርሱ። ማይክል ጃክሰን በፖፕ ስልት ሰንጠረዥ ላይ ቁጥር አንድ ላይ መቀመጥም ጀመረ።
ኋላም ከሞቶውን ሪከርድስ (Motown Records) ጋር የነበራቸው ህብረት ፈርሶ ጃክሰንስ ቀጠለ።
በ1971 ዓ.ም. ‘’Off the Wall’’ የተሰኘ አልበሙን ያወጣው ማይክል ጃክሰን በስራው ኮከብ ለመባል በቅቷል። ከግምቶች በላይ መሆን የቻለው ይሄው የመጀመሪያ አልበሙ በወጣበት አመት በትልቁ የተሸጠ አልበም ለመሆን ችሏል። 20 ሚሊዮን ሽያጭ አስመዝግቧል።
“Thriller” የተሰኘ አልበሙንም ደገመ። እ.ኤ.አ. በ1982 የወጣው ይሄው አልበሙ የምንጊዜም ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ አልበም ሆነ። 40 ሚሊዮን ሽያጭም አስመዝግቧል። እ.ኤ.አ. በ1987 ያወጣው ‘’Bad’’ የተሰኘው አልበሙ ደግሞ በአሜሪካ የቢልቦርድ ሰንጠረዥ ቁጥር አንድ ላይ መቀመጥ የቻለ አልበም ነው።
የተለያዩ ክሶች ውዝግብ የገጠመው ቢሆንም ማይክል ጃክሰን የፖፕ የሙዚቃ ንጉስነቱን አስጠብቆ መቀጠል ችሏል።
ጃክሰን ሙዚቃዎቹ በሰፊው የተሸጡለት ሙዚቀኛ ነው። ሙዚቃዎቹ በዓለም ዙሪያ 400 ሚሊዮን ያክል ሽያጭ እንዳስመዘገቡ ይገመታል። በቢልቦርድ ሰጠረዥ ከተቀመጡ 100 ቀዳሚ ሙዚቃዎች 13ቱ የጃክሰን ስራዎች ናቸው።
በሌላ በኩል በቢል ቦርድ የሙዚቃ ሰጠረዥ በአምስት የተለያዩ አስርት አመታት ምርጥ 10 ነጠላ ዜማዎች ውስጥ ስራዎቹ የተካተቱለት ብቸኛው ሙዚቀኛም ነው።
የምንጊዜም በዓለም አቀፍ ዙሪያ ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ ሙዚቀኛ ለመባል የበቃው ማይክል ጃክሰን ከተሰጡት ሽልማቶች 15 የግራሚ ሽልማቶችን ማሸነፍ ችሏል። 6 የብሪት ሽልማትን፣ አንድ የጎልደን ግሎብ ሽልማትን ጨምሮ 39 የጊነስ ዎርልድ ሪከርድን በእጁ ማስገባት ችሏል።
በ1977 ዓ.ም. ጃክሰን እና ልዮኔል ሪቼ ‘’We are the world’’ የተሰኘ ሙዚቃን ጽፈዋል። ይሄው ሙዚቃ አሜሪካ ለአፍሪካ በሚል የረሃብ እፎይታ ለማምጣት ያለመ ፕሮጀክት አካል ነበር። በሀገራችን ኢትዮጵያ በጊዜው ለተከሰተውን ረሃብም የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ፕሮጀክት ነበር።
ዓለምን በዳንሶቹ በታጀቡ የሙዚቃ ስራዎቹ ያስደመመው ማይክል ጃክሰን በ2001 ዓ.ም. ቢያርፍም ዛሬም የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ተብሎ በሙዚቃ አፍቃሪያን መጠራቱ አልቀረም።
በአብርሃም በለጠ
2022-07-07
