በዚህ ዘመን በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን ለማፍራት ችለዋል።
በተለይ ታዳጊዎችና ወጣቶች እነዚህን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በስፋት ይጠቀሙባቸዋል።ገጾቹም በዋናነት ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ አዳዲስ አገልግሎቶችን እያቀረቡ ነው።
በዚህም ሳቢያ በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ፋይዳ በሌላቸው ጉዳዮች ሰፊ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።በዓለማችን የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ ቁጥር ከሶስት ቢሊየን በላይ እንደሚሆን ይገመታል።አብዛኛዎቻችን ደግሞ ከአንድ በላይ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን እንጠቀማለን።
በአማካይም ከ2 እስከ 3 ሰአት በእነዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እናጠፋለን። ሀገሬ ቴሌቭዥንም ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ከሁለት ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል ።
ሰለሞን አበጀ (ዶክተር) የባህርዳር ዩንቨርስቲ የፎክለር ትምህርት ክፍል መምህር ፦ አይምሯቸን አንድን ነገር ብቻ እንዲያስብ እያደረገን ነው ባይ ናቸው ቅጥ ያጣው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን በማስታወስ ችሎታችን ላይ ተስጸኖ እያደረሰብን ነው ሲሉ ዶ/ር ሰለሞን ተደምጠዋል።
የስነ ጽሁፍ መምህር የሆኑት አቶ መሰረት አበጀ በበኩላቸው በማህበራዊ ሚዲያ የምናገኛቸው ልጥፎች አጫጭር በመሆናቸው የታተሙ መጽሃፎችን ለማንበብ ትዕግስት እያሳጣን ነው ብለዋል ፡፡
ይህው የማህበራዊ ሚዲያ የእርስ በእርስ ግንኙነታችንንም እየጎዳው እንደሆነ ዶ/ር ሰለሞን ይናገራሉ። ማሕበራዊ ሚዲያ ጉዳት አለው ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል ይልቁንም አጠቃቀሙ ላይ ልናውቅበት ይገባል ሲሉመምህራኑ ተደምጠዋል።
በመቅደስ እንዳለ
2022-07-07
