ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ይፋዊ ጦርነት ካመሩ ዛሬ 139ኛ ቀንን አስቆጥረዋል፣ በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን፤ በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት መውደሙን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመላክታል።
ጦርነቱ ከዛሬ ነገ ማብቂያውን ያገኛል ቢባልም በየሰዓቱ፣ በየዕለቱ ከሁለቱም ወገን የሚውጡ መርጃዎች ውጥረቱን እያባባሱት ነው ይላሉ የብዙሃን መገናኛ መረጃዎች።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ለዩከሬን ዜጎች ፓስፖርት እሰጣለሁ” ማለታቸውን ተከትሎ ዩክሬን እና አጋሮቿ ተቃውሞዋቸውን እያሰሙ ነው።
ሚያዝያ 27 ላይ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቤጂንግን በጎበኙበት ወቅት ሩሲያ ሁሉም ዩክሬናውያን የሩሲያ ዜግነት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ እንደሚያመቻቹ ገልጸው ነበር፤ ከወሬ አያልፍም በሚል እንዳለስማ ያለፉት ማዕራባዊያኑ አሁን ጩኸታቸው በርክቷል።
ሞስኮ ከዚህ በፊት በሩሲያ ቁጥጥር ሥር በዋሉ የዩክሬን ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ፓስፖርት ስትሰጥ መቆየቷ አይዘነጋም። አሁን ደግሞ ለሁሉም የዩክሬን ዜጎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው የፕሬዚዳንት ፑቲን መንግሥት አውጇል።
አዲሱ አዋጅ ዓላማ ያደረገው በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር በዋሉ የዩክሬን ግዛቶች ለሚገኙ ዜጎች የተፋጠነ አገልግሎትን መስጠት ነው።
ፕሬዚዳንቱ ትላንት እውን ያድርጉት እንጂ ይህንን ውጥን ከ3 ዓመታት በፊት ቃል ገብተውም እንደነበር ንግግራቸው ያመላክታል።
“በሩሲያ ለሚኖሩ ሰዎችን ብቻ አይደለም፤ በሉሃንስክና በዶኔስክ ለሚኖሩት ጭምር የሩሲያነን ፓሰፖርት እንሰጣለን፣ በተጨማሪም ሁሉም የዩክሬን ነዋሪ የሩሲያን ፓስፖርት ማግኛ መንገድ እንዲቀል እናደርጋለን።”
ፕሬዚዳንቱ የፈረሙት አዋጅ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙት የዛፖሪዢያ እና ኬርሰን አካባቢ ነዋሪዎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል።
ዶንባስ በመባል በሚታወቁት በሉሃንስክና በዶኔስክ ክልሎች ቀደም ሲል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ከ2011 ዓ.ም ወዲህ የሩሲያ ዜግነት አግኝተዋል።
ቀድሞውንም የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ የማያሰደሰታቸው እና ከዩክሬን ጎን ነን የሚሉት ምዕራባዊያን ሀገራት ተቃውሞዋቸው በዝቷል።
አሜሪካም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በኩል ባወጣችው የተቃውሞ መግለጫ ሩሲያ ዩክሬናውያንን በግድ ለማስገበር እየሞከረች ነው በማለት ከሳለች።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ የፓስፖርቱ አዋጅ የፑቲን "የማጥመድ ፍላጎት" ምሳሌ በመሆኑ የዩክሬን አጋሮች ወታደራዊ እርዳታ እንዲጨምሩ እና በሩሲያ ላይ አዲስ ኢኮኖሚያዊ ቅጣቶችን እንዲጥሉ ጠይቀዋል።
ሐምሌ 04 በወጣው መግለጫ ላይ “የዩክሬንን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት የሚጋፋ ከዓለም አቀፉ ሕግ ደንቦችና መርሆዎች ጋር የማይጣጣም ሌላ ጥሰት ነው” ይላል።
ይህ መስፋፋት የሩሲያ የሥራ እቅድ ምንም የመልክዓ ምድራዊ ገደብ እንደሌለው የገለጹት በኪዮቭ የሚገኘው የዴሞክራቲክ ኢኒሼቲቭስ ፋውንዴሽን የምርምር ተቋም የክልል ደህንነትና ግጭት ጥናት ኃላፊ የሆኑት ማሪያ ዞልኪና ናቸው።
የዩክሪን ባለሥልጣናትም ሆኑ ሌሎች ሀገራት የመግለጫ ጋጋታ ቢያውጡም ታስ የተሰኘው የሀገሪቱ ዜና አገልግሎት እንዳስነበበው ከሆነ በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊርማ በወጣ አዋጅ ከዚህ በፊት በከፊል ለዩክሬን ዜጎች ብቻ ይሰጥ የነበረው የሩሲያ ፓስፖርት ለሁሉም ዩክሬናዊያን ይሰጣል የሚለውን መርጃ ሲያሰራጭ ውሏል፡፡
በፍሬሕይወት ታደሰ
2022-07-12
