ሱስ የሚለው ቃል በራሱ አሉታዊ ወይንም ትክክል ያልሆነ ነገርን ይይዛል። ለዚሁ ቃል ትርጓሜ ፍለጋ ስንወጣ፤ ሱስ ማለት ደስታን ለማግኘት የምናደርገው አልባሌ ነገር ወይንም ጥገኛ ያደረገን ደስታን ለማግኘት የምንጠቀመው ነገር ነው ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።
ለአብነትም ደስታን ይሰጠኛል እያሉ ሲጃራን የሚጠቀሙ፣ እንደ አደንዛዥ ዕጾች አይነቱን የሚወስዱ እና ሌሎችም በሰዋዊ መንገድ ሊሰሙ የሚገቡ ስሜቶችን በአቋራጭ የሚያቀብሉን እና ለሰውነታችን በሽታንም የሚያስታቅፉን አይነት።
ዘወትር እንድናደርጋችው የሚያስገድዱን አላስፈላጊ ዝንባሌዎች አልያም ድርጊቶች ሱስ ተብለው ይጠራሉ። እንደው በልማድ እንደ ንብብ፣ በጎ ማድረግ፣ እና ሌሎች መልካም ነገሮችን ደጋግሞ የማድርግ ዝንባሌ ያለውንም ሰው ሱስ ይዞታል ቢሉም ትርጓሜው ለምግባሩ የገጠመ አይደለም።
እዚህ ጋር ነው መታረም የሚገባን እነዚህ መልካም ነገሮች የህይወት መንገዳችን አንድ አካል ሊሆኑ የሚገባቸው ነገሮች ስለሆኑ።
ስለዚህ ሱስ በሚለው ቃል ትርጓሜ ላይ ተግባብተናል ማለት ነው።
ታዲያ እኛም ለወትሮ ከምናውቃቸው አይነት የተለየ ነገር ሱስ ሆኖ ህግ ወጥቶለት እየተተገበረ ነው መባሉን ሰምተናል።
ሶማሊ ዜጎቼ በጉንዳን ሱስ ተጠምደውብኛል ስትል ህግን አውጥታለች። ህጉ ሶማሊዎች ሱስ ሆኖባቸዋል ያለችውን ጉንባንን መጠቀም የሚከለክል ነው።
ሶማሊያውያኑ ይህንን ጉንዳን በመቀቀል እንፋሎቱን ይታጠኑታል። ከዚያ በኋላማ በቃ በራሳቸው ዓለም ውስጥ መዋለል ይጀምራሉ።
ታዲያ በዚህ የተማረረው የሱማሊ መንግስት ጉንዳኑን ከአደንዛዥ ዕጾች ተርታ መድቦታል። ተተቅሞ የተገኘ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ እያስጠነቀቀም ይገኛል።
ይህ የፈረደበት የጉንዳን ዝርያ ታፒኖማ ሰሲል ሲሉ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይጠሩታል። ሳይንሳዊ መጠሪያው ነው። የህክምና ባለሙያዎች ጉንዳኑ ፎርሚክ የተሰኘ አሲድን የሚያመነጭ መውና ለጤና ጠንቅ ነው እያሉ ይገኛሉ።
በሰዎች ላይ ማቅለሽለሽ፣ ማዞር እና ሌሎች የህመም ስሜቶችን ያስከትላል። ይህንን ጉንዳን አብዝተው የተመገቡ አዕዋፍት ሰክረው መላቅታቸውን ሲያጡ ይስተዋላሉ።
ሰዎችም ይህንኑ ስሜት ፍለጋ ጉንዳኑን መታጠን ስራቸው አድርገውታል ሲሉ አንድ የሀገሬው የፖሊስ አዛዥ ለሱማሊ ኬብል የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
ይህ የጉንዳን ዝርያ ሰዎች ጎጇቸውን ቀልሰው በሚኖሩበት አቅራቢያ በብዛት ይገኛሉ። ከመሬት በታች የተወሳሰበ እና የተደራረበ መኖሪያን ሰርተው ይኖራሉ።
የሱማሊ ሰዎችም አብዝተው እነዚህን ጉንዳኖች በመጠቀማቸው ሳቢያ የጉንዳኖቹ ቁጥር ቀንሷል መባሉም ተዘግቧል። ሶማሊያውያኑም ጉንዳኖቹን ፍለጋ በየቦታው መዞራቸውን መቀጠላቸውንም ዘገባው ሳያትተው አላለፈም።
በሳምሶን ገድሉ
2022-07-12
