መቼም ይህ ኮቪድ ቫይረስ ያላመጣው ጉድ የለም። የለመድናቸውን ነገሮች ከለመድናቸው መንገዶች ውጪ እንድናደርግ አስገድዶናል።
ኮቪድ እንድንለምደው ካደረጋቸው ነገሮች መካከል ዋነኛው የኦንላይን ትምህርት ነው። በዘመነ ኮቪድ ተማሪው በቤቱ ተቀምጦ ትምህርቱን በገዛ ኮምፒውተሩ ይኮሞኩማል።
ታዲያ ይህ የኦን ላይን ትምህርት በነበረው ትቅም ልክ እንደ መደበኛው ትምህርት ስርዓት ተማሪዎችን ለመቆጣጠር ከበድ ያለ ነበር የሚሉ በርካቶች ናቸው።
ይህ የትምህርት መንገድ በማስበው ልክ እንዳስተምር አላደረገኝም ያለ አንድ መምህር አደረገ የተባለው ነገር ግርምትን ቢያጭርብን እንዲህም አለ ልንላችሁ ወደድን።
ነገሩ ከወደ ህንድ ነው ። ኑሮውን በመምህርነት ይገፋ የነበረ አንድ ግለሰብ የ ኮቪድ ወቅት በገባ ጊዜ ተማሪዎችን በበይነ መረብ ወይም በ ኦንላይን እንዲያስተምር ይታዘዛል ።
ታዲያ ይህ ሰው ስራውን ጠንቅቆ የሚሰራ ነውና በተባለው ሰአት የማስተማሪያ ቁሳቁሶችን አዘጋጅቶ ተማሪዎችን በበነመረብ እንዲገኙ መጠበቅ ይጀምራል ።
ነገር ግን በመጀመሪያ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ለመከታተል የተገኙ ተማሪዎች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። መምህሩ ምን አልባት መረጃው አልደረሳቸው ይሆናል በሚል የመጡትን አስተምሮ ተለያዩ። በቀጣይ ቀናትም በሰዐቱ ተገኝቶ መጠበቅ ቢጀምርም የመምህሩን ትምህርት ለመከታተል የሚፈልግ አንድም ተማሪ አልተገኘም ።
ይህ ሰው የ ኮቪድ ትርምስ ተረጋግቶ ወደ ተለመደው የትምህርት ስርዐት እስኪመለስ በሰዐቱ ተገኝቶ ተማሪዎቹን ቢጠብቅም አንድም ተማሪ የሱን ትምህርት ለመከታትል የሚመጣ አልነበረም ።
በዚህ ሂደት ውስጥ የ ኮቪድ ወቅት አልፎ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ተደረገ ። ታዲያ ያለፉት ሁለት አመታት ይህ መምህር በተማሪዎቹ በጣም የተከፋበት እንዲሁም ያዘነበት ጊዚ ነበሩና ወደ ትምህርት ቤቱ አስተዳደሮች በመሄድ አንድ ነገር አደረገ ። ትምህርት ቤቱ ላለፉት ሁለት አመታት የከፈለውን 1,560,330 ብር ደሞዝ ይህ ያለስራሁበት ነዋና እባካቹ ተቀበሉኝ አለ ።
አስተዳደሮቹ በግለሰቡ ድርጊት ተገርመው ለምን ሲሉ በጠየቁት ጊዜ በ በበይነ መረብ እንዳስተምር በተሰተኝ ትዕዛዝ ተማሪዎችን ብጠብቅም የኔን ትምህርት ለመማር ፈልጎ የመጣ አንድም ተማሪ አልነበረም ነገር ግን ትምህርት ቤቱ በየ ወሩ የሚያስገባልኝ ደሞዝ ስራውን በአግባቡ ሰርትዋል ብሎ ነውና ህሊናዬ እረፍት አጣ ሲል መለሰለላቸው።
የሚያስገርመው ትምህርት ቤቱ የ መምህሩን ክስ ውድቅ አድርጎ ገንዘቡን አልቀበልም ማለቱ ነው ። ይባስ ብሎም ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን በ አግባቡ ተከታትለዋል ብሎ ወደቀጣይ ክፍል አሳልፈዋቸዋል ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-07-13
