የኤርትራ እና የሶማሊያ መሪዎች የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ትብብርን የሚመለከት ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውቀዋል።
በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ መካከል ስምምነቱ የተደረሰው አዲሱ የሶማሊያ መሪ ለአራት ቀናት አስመራ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ነው።
ሀገራቱ ማክሰኞ የፈረሙት ሰነድ ሰላምን፣ መረጋጋትንና ደህንነትን ለማስጠበቅ የመከላከያ እና የጸጥታ ትብብርን ለማጠናከር ነው ብለዋል።
ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር፣ አገራዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ እንዲሁም የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ለማሳደግ ተስማምተዋል ብለዋል ።
ዛሬ ላይ እዚህ የደረሰው የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ትላንት እንዲህ የሚታወስ አልነበረም።
ሳማሊ በጉያዋ ሆነው እረፍት ለሚነሳት አሸባሪው አልሸባብ ጉልበት መፈርጠም ኤርትራን ተጠያቂ ስታደርግ ነበር። ይህንን የታከኩ የዲሞክራሲ ጠባቂ ነን የሚሉት ምዕራባውያን ሀገራትም የማዕቀብ ናዳ በሀገረ ኤርትራ እና መሪዋ ላይ ለመጣል ከልካይ አልነበራቸውም።
በዚህም ሳቢያ ኤርትራ በሱማሊ ላይ ጥርሷን ነክሳ ቆይታለች።
በወርሀ ሐምሌ 2010 ዓ.ም ለመጀሚያ ግዜ የቀድሞው የሶማሊው ፕሬዚዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ መሀመድ ፎርማጆ አስመራ ተገኙ። ከኤርትራው አቻቸው ኢሳያስ አፍወርቂ በአስመራ ከተወያዩ በኋላ ፊርማቸውን በተግባቡባቸው ሰነዶች ላይ አኖሩ።
ያኔ የሁለቱ ሀገራት ወዳጅንት ትላንቱን ረስቶ አዲስ ምዕራፍን አንድ ብሎ ጀመረ። በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም ሶማሊ የሀገሯ ወታደሮች በኤርትራ መሬት ላይ ሄደው ወታደራዊ ትምህርት እንዲቀስሙ አደረገች። ሁለተኛዎቹ ዙር ወታደሮች ክረምቱን ተሻግረው በጥቅምት 2012 ዓ.ም አስመራ ደርሰዋል።
አሁን በቀይ ባህሯ አገር ወታደራዊ ስልጠናን እየወሰዱ ካሉት የሱማሊ ጦር አብዛኛው መደበኛ እና ልዩ ስልጠና የወሰደው ነው።
በኤርትራ የሰለጠኑት የሶማሊ ወታደሮች ቁጥር 5,167 መሆኑን ቪኦኤ ዘግቧል። በሶማሊ የስለላ ድርጅት የሚመራ ስለመሆኑም የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ ይሄው የዜና ተቋም አስነብቧል።
በዚህ ሁሉ መሀል ነው እንግዲህ የሱማሊው አዲሱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ጉብኝታቸው ወደ ኤርትራ ያደረጉት።
ከብዙኃን እይታ ተሰውሮ ለነበረው ጦራቸው ባደረገው ሰልፍ ላይ ተገኝተው የውትድርና ስልጠና በማጠናቀቃቸው እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
የፕሬዝዳንቱ ፅህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ መሰረት መሀሙድ ወታደሮቹን ወደ ሶማሊያ ለመመለስ የገቡትን ቃል በማደስ ሀገሪቱን ለማረጋጋት እና አሁንም በአልሸባብ ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎችን ለማስለቀቅ ስላለው እቅድ እንደነገራቸው ተናግሯል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-07-13
