ሀገሬ ቲቪ

እንድትበር ታሰባ የነበረችው ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ

የመጀመሪያዋ ባለሶስት እግር ዳይማክሲን የተሰኘችው ተሽከርካሪ የተነደፈችው አርኪቴክት፥ ኢንጂነር እና አሳቢ በነበረው በክሚኒስተር ፉለር ነው፡፡ ይህችው በዘመኑ ለየት ያለችው ተሽከርካሪ የተመረተችው በዛሬዋ እለት በ1925 አ.ም. በኮኔክቲከት ነበር፡፡

ፉለር ውልደቱ በ19ነኛው ክ/ዘ መጨረሻ በአሜሪካ ማሳቹሴት ነው፡፡ ፉለር ራሱ እንደሚለው ግለሰብ አለምን ለመቀየር እና ሁሉንም ሰው ለመጥቀም አስተዋጽኦ ለማድረግ ህይወቱን ቤተሙከራ አድርጓት ነው የኖረው፡፡

'Dynamic'፥ 'Maximum' እና 'አየን' ከሚሉት የእንግሊዘኛ ቃላትም ''Dymaxion" ያለውን ቃል ፈጥሯል፡፡ ለፈጠራዎቹም ይሄን ስያሜ ሰጥቷቸዋል፡፡

ዳይማክሲን ካላት ተሽከርካሪ በተጨማሪም ዳይማክሲን ያለውን የቤት ፈጠራውን አበርክቷል፡፡ ይሄው የቤት ፈጠራው ቀላል ክብደት ካለው አልሙኒየም በመሰራቱ ካንዱ ቦታ ወደሚፈለገው ቦታ በአየር መጓጓዝ የሚችል ነበር ፡፡

ፉለር በ1920ዎቹ መጀመሪያ ዳይማክሲን የተሰኘችውን ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ፎር ዲ ትራንስፖርት (4D Transport) በሚል ስያሜ ነደፋት፡፡ ግማሽ አውሮፕላን ከፉል ተሽከርካሪ የሚያስመስላት ክንፍም ነበራት። ከብዙ ማሻሻያዎች እና ማማከር በኋላ የመጨረሻ ያለውን ቅርጿን እንድትይዝ ተደርጓል ።

በመጨረሻም ይህችው ዳይማክሲን የተሰኘችው ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ተመርታ ለ38 አመቱ የፈጠራ ባለቤቷ ፉለር ከ89 አመታት በፊት በዛሬዋ እለት ቀረበች። ይህችው ከብረት ክፍሎቿ የተሰሩት ተሽከርካሪ የአልሙኒየም ሽፋን የነበራት ሲሆን 128 ኪ.ሜ በሰአት መጓዝ የምትችል ነበረች።

ለገልፍ ኦይል የተሸጠችው ዳይማክሲን በቺካጎ ለእይታ ቀረበች። ግና በማሽከርከር የተካነው ፍራንሲስ በርነር ተሽከርካሪዋን ለህዝብ እያስተዋወቀ ባለበት ሰአት በደረሰ አደጋ ህይወቱ አለፈ፡፡ ምርመራዎች ዳይማክሲንን ከተጠያቂነት ነጻ ቢያደርጓትም ባለሃብቶች ግን እርሷን ለማምረት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡

ነገር ግን ይህችው በ1920ዎቹ የተሰራች ልዩ ተሽከርካሪ ምንም እንኳን በብዛት ለመመረት ባትታደልም በዘመኑ አዲስ አይነት የተሽከርካሪዎች ንድፎች እንዲታሰቡ ብሎም ቅቡልነት እንዲኖራቸው አይን መክፈት ችላለች፡፡

በ2000 አ.ም. ብቸኛዋ ተርፋ መገኘት የቻለችው የዳይማክሲን ተሽከርካሪ በኒው ዮርክ ከተማ በዊትኒ ሙዝየም በፉለር ስራነት እንድትቀመጥ ተደርጓል።

በኤግዚቢሽኑ ላይ በኒውዮርክ ታይምስ የታተመ አንድ መጣጥፍ ፉለር ፈጠራውን “ሁሉም ሰው መኪና ብለው እንደሚጠሩት አውቅ ነበር” ሲል በወቅቱ ስለ ዳይማክሲን የተናገረውን አስታውሶ ነበር ።

በዮሴፍ ከበደ
2022-07-12