የጥቁሮች ህይወት ይገደኛል “Black Lives Matter” ይሉት እንቅስቃሴ ጥቁሮች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማውገዝ የተፈጠረ እንቅስቃሴ ነው። የእንቅስቃሴው ጅማሮ ታዲያ ከአስር አመታት በፊት ወዳለ ሁነት ይመልሰናል።
ትሬይቮን ማርቲን የተሰኘ አፍሪካ አሜሪካዊ ወጣት በተኩስ ተገደለ። ይሄው የ17 አመት አዳጊ ወጣት የተገደለው የጀርመን እና ፔሩ ውሉድ የሆነ ጆርጅ ዚመርማን በተሰኘ የፍሎሪዳ ሰው ነበር። የኢንሹራንስ ማጭበርበር መርማሪ የነበረው ዚመርማን በጥርጣሬ ለፖሊሶች ካመለከተ በኋላ ምንም እንዳያደርግ ቢነገረውም የጦር መሳሪያ ያልያዘውን ዘመድ ለመጠየቅ የሄደውን ማርቲንን ተኩሶ በሳንፎርድ ፍሎሪዳ ገደለው።
ግና ደግሞ ዚመርማን ቢታሰርም ራሱን ለመከላከል ያደረገው ነው በሚል በነጻ ተለቀቀ። ይሄው ሁነት ነበር አሊሽያ ጋርዛ የተሰኘችን አሜሪካዊት የካሊፎርኒያ ነዋሪ በፌስ ቡክ ገጿ ሀዘኗን እንድትገልጽ ያደረጋት። በፌስቡክ ገጿ “Black Lives Matter” የሚለውን ሀረግ በዛሬዋ ዕለት በ2005 ዓ.ም. አሰፈረች።
ጋርዛ የማርቲን ገዳይ ዚመርማን በነጻ መለቀቁ ጥልቅ ሀዘን አስከተለብኝ። ይበልጥ ደግሞ ተጠቂው ማርቲን ስለመሞቱ ተጠያቂ ያደረገው የዘረኝነት በሽታ ሀዘኑን እንዳባሰባት ትገልጻለች። የጥቁሮች ህይወት ይገደኛል የ “#BlackLivesMatter’’ እንቅስቃሴ ጀመረ። አንድ ያለው ግን የጋርዛ ጓደኛ የሆነችው እና በሎስ አንጀለስ የማህበረሰብ አደራጅ የሆነችው ፓትሪስ ኩለርስ ለአሊሽያ ጋርዛ ልጥፍ ምላሽ በመስጠት ነበር። ይሄው እንቅስቃሴ የአሜሪካን ብሎም የዓለምን ማህበራዊ መገናኛዎች አዳረሰ።
በማህበራዊ መገናኛዎች ፌስ ቡክ እና ትዊተር እንቅስቃሴው ሰፊ እውቅና ካገኘ በኋላ አላይሽ ጋርዛ፣ ፓትሪስ ኩለርስ እና የማህበረሰብ አንቂዋ ኦፓል ቶሜቲ የማህበረሰብ እንቅስቃሴ ትስስርን አደራጁ። ይሄንንው ትስስርም ‘’Black Lives Matter’’ ሲሉ ሰይመውታል።
ይሄው ግዙፍ የጥቁሮች መብት እንቅስቃሴ በማህበራዊ መገናኛ እንቅስቃሴዎቹ እና ሰልፎቹ ሳቢያ የማርቲን ገዳይ ዚመርማን እንደገና እንዲታሰርም ምክንያት ሆኗል።
ይሄው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በማህበረሰብ አንቂዎች እና የጥቁሮች የመብት ጥሰት ተቃዋሚዎች እንዲስፋፋ ሆኗል። በተጨማሪም የሚካኤል ብራውን፣የኤሪክ ጋርነር እና ሌሎችም የአፍሪካ አሜሪካውያን በፖሊሶች መገደል እንቅስቃሴውን የበለጠ እንዲበረታ አድርጎታል።
የጥቁሮች ሰብዓዊ ክብር ይጠበቅ የሚል ፍላጎት ያለው እንቅስቃሴው ‘’Black Lives Matter’’ የምትለዋ ሀረግ ዓለም አቀፋዊ እውቅ የተቃውሞ ምልክት እንድትሆን አድርጓታል።
በተለይም ደግሞ በ2008 ዓ.ም. የብራውን በፈርጉሰን ሚሶሪ በፖሊስ መገደል እንቅስቃሴውን ከፍ እንዲል አድርጎታል። በአሜሪካም ቢሆን የህዝብ አስተያየት መረጃዎች እንደሚያመላክቱት እንቅስቃሴው ሲጀመር አካባቢ ብዙም ቅቡል ያልነበረ ቢሆንም በጊዜ ሂደት የእንቅስቃሴው ደጋፊዎች ቁጥር ጨምሯል።
የ2012ቱ በሚኒያፖሊስ የጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ መገደል ደግሞ እንቅስቃሴውን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጎታል።
“ብላክ ላይቭስ ማተር’’ ይሏት ሀረግም በአሜሪካ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ የዘረኝነት ብሎም የፍትህ ንፍገት ተቃውሞ ምልክት ሆና ዘልቃለች።
በአብርሃም በለጠ
2022-07-13
