ሀገሬ ቲቪ

የቦሪስ ጆንሰን ስልጣን መልቀቅ ዩክሬናውያንን አሳዘነ

በብሪታንያ ፓርላማ የወግ አጥባቂው ፓርቲ አባላት ባለፈው ሳምንት ከስልጣን እንደሚለቁ ያሳወቁትን የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ፖለቲከኛ ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት የሚወዳደሩ ሁለት እጩዎችን ይመርጣሉ። በበርካታ ቅሌቶች ሲከሰሱና ሲወቀሱ የቆዩት ጆንሰን እስከ ሐሙስ ድረስ ከወንበራቸው ላለመነሳት ብዙ ጥረዋል።

ጆንሰን በመግለጫቸው በስልጣን ዘመናቸው በተለይ ብሬግዚት መሳካቱንና በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ከሌሎች የአውሮጳ ሀገራት በፈጠነ መንገድ በብሪታንያ የኾቪድ 19 መከላከያ ክትባትን ማዳረስ መቻሉን “የምኮራበት የዚህ መንግሥት ስኬት ናቸው” በማለት አወድሰዋል።

ይሁንና የ58 ዓመቱ ጆንሰን በስልጣን ዘመናቸው አሳካኋቸው ያሏቸው እነዚህ ተግባራት በስተመጨረሻ ከስልጣን ተገደው ከመውረድ አላዳኗቸውም።

ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ዘመናቸው አሳካኋቸው ካሏቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ ብሪታንያ ከዩክሬን ጎን እንድትቆም ማድረጋቸው እንደሆነ ይነሳል፤ ከዚህ ቀድም በሚያዚያ ወር ባደርጉት ንግግር ዩክሬን በምትሻቸው ማንኛውም ድጋፎች ብሪቴን ከጎኗ እንደሆነች አረጋግጠው ነበር።

“የኢኮኖሚ ድጋፍም ሆነ ከዚያም ውጪ የተደራጀ ወታደራዊ ድጋፍም የምትፈልጓቸውን ነገሮች ለመስጠት ዝግጁ ነን፤ ይህንን ስል ኩራት ይሰማኛል ፤ ብሪቴን ሁሌም ከዩከሪን ጎን ትቆማለች።”

ጆንሰን ከለቀቁ በኋላ ከዩክሪኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሜር ዜሌንስኪ ጋር ባደርጉት የስልክ ንግግር ዜሌንስኪ “ይሄንን ዜና ሁላችንም በሀዘን ሰምተናል፤ እኔ ብቻ ሳይሆን መላው የዩክሬን ኅብረተሰብም ጭምር አዝኖል” ብለዋል።

የ44 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ “የታላቋ ብሪታኒያ ድጋፍ ተጠብቆ እንደሚቆይ ምንም ጥርጥር የለንም ነገር ግን የእርስዎ የግል አመራርና ተአምራት ልዩ ያደርጎታል” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

ከዚሀ ዓመት በፊት የብሪታንያ ፖለቲካ ለዩክሬን ሕዝብ አሳሳቢ ነበር፤ የአውሮፓ ህብረት ጋር ለመቀላቀል የሚፈልጉ ዩክሬናውያን ብሪኤግዚትን ሙሉ በሙሉ አልደገፉም፤ ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ በዚህ ዓመት ተለውጧል ።

በየካቲት ወር መገባደጃ ላይ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጆንሰን ዩክሬንን በመደገፍ ከፍተኛ ድምፅ ካላቸው የዓለም መሪዎች ዋነኛው ሆነዋል።

ድጋፉ በአፍ ብቻም አልነበረም በገንዘብ እንጂ፤ የብሪታንያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ መሰረት ብሪታንያ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለዩክሬን 2.3 ቢሊዮን ፓውንድ (2.77 ቢሊዮን ዶላር) ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች። ከዩናይትድ ስቴትስ በስተቀር የብሪታያ ድጋፍ ከማንኛውም ሌላ ሀገር በእጅጉን ይበልጣል።

ይህ ግንኙነት ጠበቆ በሚያዝያ ወር ጆንሰን ኪየቭን ከጎበኙት የመጀመሪያዎቹ የዓለም መሪዎች አንዱ ሆኑ። ታዲያ ይህ ጉዞ በዩክሬን እንደ ጽኑ አጋር እና በሕዝብም አእምሮ ውስጥ ያለውን አቋም የሚያጠናክር እርምጃ ነበር።

በቅርቡ በሎርድ አሽክሮፍት የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው 90 በመቶ የሚሆኑት ዩክሬናውያን ለጆንሰን አዎንታዊ አመለካከት አላቸው ከቅርብ ወራት ወዲህ እንደውም የዩክሬን ከተሞች በሚገኙ ጎዳናዎችን ስም በጆንሰን እንዲሰየም ሐሳብም ጭምር አቅርበዋል።

ታዲያ አሁን ላይ ጆንሰንን ለመተካት ወግ አጥባቂ ፓርቲ ላቀረበው የመሪነት የእጩዎች ውድድር እያደረገ ነው፤ ወግ አጥባቂውን ፓርቲ በብሪታንያ ፓርላማ የሚወክሉ 358 እንደራሴዎች በሚሰጡት ድጋፍ መሠረት የሚያልፉት እያለፉ ሁለት እስኪቀሩ ድረስ ውድድሩ ይቀጥላል።

ከሁለቱ እጩዎች አንዱን መስከረም መጨረሻ ላይ የወግ አጥባቂው ፓርቲ 200 ሺህ አባላት በደብዳቤ እንዲመርጡ ይደረጋል። አሸናፊውም ቦሪስ ጆንሰንን ተክቶ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል።

ለመጨረሻው ውድድር ይደርሳሉ ተብለው የሚጠበቁት የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትር ራሺ ሱናክና ባለፈው ምርጫ ከቦሪስ ጆንሰን ጋር ተወዳድረው የተሸነፉት ጀርሚ ሀንት ናቸው። ያኔ ቦሪስ ጆንሰን ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት አባልነት እንድትወጣ ፣ሀንት ደግሞ ሀገሪቱ በአውሮፓ ኅብረት ስር እንድትቆይ ሲከራከሩ ነበር።

በአሁኑ ጊዜ ግን አብዛኞቹ ተንታኞች የሀገሪቷ የዩክሬን ስትራቴጂ ሊቀየር ይችላል አይችልም በሚለው ላይ መከራከሪያ ቢኖርም ድጋፍ እንኳ ቢኖር እንደቦሪስ ጆንሰን አይሆንም የሚል ስጋት አንዣቧል።

በመላው ዓለም በሚያስብል ሁናቴ ፖለቲከኞች ዩክሬንን ይደግፋሉ። በእርግጥም ዩናይትድ ስቴትስ ሀገሪቱ ሩሲያን እንድትቃወም ለመርዳት ባላት ቁርጠኝነት ከጆንሰን ቀዳሚነት ስፍራ ትይዛለች።

በፍሬሕይወት ታደሰ
2022-07-14