ሀገሬ ቲቪ

የቴሌግራፍ መሰናበት

የመጨረሻው የቴሌግራፍ መልዕክት በህንድ በዛሬዋ ዕለት በ2005 ዓ.ም. ከተላከ በኋላ የቴሌግራፍ አገልግሎት ተቋርጧል። ቴሌግራፍ በርቀት መልዕክት የመቀባበያ መንገድ ሆኖ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ አገልግሏል።

በእኛም ሀገር ቢሆን ከአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በ19ነኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ከሀረር አዲስ አበባ መልዕክት በማስተላለፍ የጀመረው የቴሌግራፍ አገልግሎት ኋላም ወደ ኤርትራ ምጽዋ፣ ጎሬ፣ ኢሉባቡር፣ ጂማ፣ ከፋ መስመሮች ተዘርግተውለት ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ ክፍሎች አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል።

ይሄው በአለም ዙሪያ የዘመናዊ የተግባቦት ቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅ መገልገያዎች አንዱ የሆነው ቴሌግራም ከመቶ አመታት በላይ አገልግሎት መስጠት ችሏል። የዚሁ ወደ ተሻሻሉ የርቀት መልዕክት መለዋወጫ ቴክኖሎጂዎች መሸጋገሪያ በመሆን ያገለገለው መሳሪያ የመጨረሻ መልዕክቱን በህንድ በዛሬዋ ዕለት እንዲያስተላልፍ ከተደረገ በኋላ ከአገልግሎት እንዲሰናበት ተደርጓል።

ቴሌግራፍ የጽሁፍ መልዕክቶችን በተዘረጋ ገመድ አልያም በሬድዮ ሞገድ ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው የህትመት መልዕክትን የሚያደርስ ቴክኖሎጂ ነበር። የዚህ መሳሪያ ግኝት ታሪክ ወደ 19ነኛው ክፍለ ዘመን መለስ ብሎ የብዙዎች እጅ እንዳረፈበት ይነግረናል።

ከብዙዎቹ አሜሪካዊው ሳሙኤል ሞርስ የተባለው ሰው በ1820ዎቹ እና 30ዎቹ ቴሌግራፍን በማበልጸግ ስሙ ይጠቀሳል። መጀመሪያ የተሰራው ይሄው ቴሌግራፍ በርቀት መልዕክት የመለዋወጥ አብዮትን አስነስቷል።

ሳሙኤል ሞርስ የቴሌግራፍ ግኝት መኖር ላይ ካደረገው አስተዋጽኦ በተጨማሪ በቀላሉ ውስብስብ መልዕክቶችን መላክ የሚያስችሉ የነጥቦች እና መስመሮች ኮዶችን ፈጥሯል።

በ1830ዎቹ አጋማሽ ደግሞ የመጀመሪያ የቴሌግራፍ መልዕክቱን ከአሜሪካ ዋሺንግተን ወደ ባልቲሞር ሜሪላንድ በተሳካ ሁኔታ መላክ ችሏል።

በአሜሪካ ለቴሌግራፍ ያለው የሰዎች ፍላጎት እና ጉጉት በፍጥነት እየጨመረ መጣ። አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማትም መቋቋም ጀመሩ። የዌስተርን ዩኘን ቴሌግራፍ ካምፓኒ (Western Union Telegraph Company) የመጀመሪያውም ነበር።

በ1850ዎቹ ደግሞ የቴሌግራፍ መስመር የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ አሜሪካ እና አውሮፓን ማገናኘት ችሏል። በተለያየ ጊዜ መሻሻሎች የታዩበት የቴሌግራፍ ግኝት ስርጭት በዓለም ዙሪያ ሆነ።

ቴሌግራፍ ጦርነቶች እንዴት እየተካሄዱ እንደሆነ ብሎም ጋዜጠኞች መረጃ የሚለዋወጡበትን መንገድ ለውጦታል። በብዙ ርቀቶች ውስጥ ገንዘብ መለዋወጥ ንግድ ማካሄድ እንዲቻል በማድረግም የራሱን ተጽዕኖ ኢኮኖሚው ላይ ማሳደር ችሏል።

በ19ነኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ሌሎች ቴክኖሎጂዎች እየተኩት ቢመጡም መጀመሪያ ላይ ተኪ ቴክኖሎጂዎቹ ከቴሌግራፍ ጋር ተመሳሳይ አሰራር ነበራቸው። ኋላም መስፋፋቱን እየገቱት እየተኩት መጡ።

ቴሌግራፍን በ21ኛው ክፍለ ዘመን የፋክስ ማሽን፣ ቴሌፎን እና ኢንተርኔት እስኪተኩት የማይናቅ ሚና የነበረው የርቀት ተግባቦት መሳሪያ በመሆን አገልግሏል። ለኋለኞቹ ለተኩት የተግባቦት ቴክኖሎጂዎች ግን መሰረት መሆን የቻለ ግኝት ነው። በዓለም ታሪክም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ትልቅ የተግባቦት ቴክኖሎጂ መነሻ ነው።

ይሄው ግኝት ታዲያ ሁለት ክፍለ ዘመናት ተሻግሮ አህጉራትን አቆራርጦ ከዘጠኝ አመታት በፊት በህንድ የመጨረሻ መልዕክቱን አስተላልፎ ከአገልግሎት በመሰናበት ታሪክ ሆኗል።

በአብርሃም በለጠ
2022-07-14