በዕለቱን ከታሪክ 84 አመታትን ወደ ኋላ መለስ ልንል ነው። በረራ ጋር የተያያዘ ታሪክን እንቃኛለን። ዳግላስ ኮሪገን የተሰኘ ልምድ ያለው አብራሪ በ1930 ዓ.ም. ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ከኒው ዮርክ ብሩክሊን ወደ አሜሪካ ካሊፎርንያ ግዛት ለመጓዝ በረራውን ጀምሯል።
ግና ኮሪገን በጉዞው አሜሪካን ለቆ ወጣ አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋረጠ 28 ሰዓታት ተጓዘ። ማረፊያውንም ሊያርፍ ካቀደበት 5 ሺህ ኪ.ሜ. ርቆ በአየርላንድ ደብሊን አደረገ።
የተሳሳተው መንገድ ኮሪገን የሚለው ስያሜም መጠሪያው ሆኗል። ይሄው ሁነት ከአስገራሚ የበረራ ታሪኮች አንዱ ተደርጎ ተምዝግቧል።
በዚህ ካሊፎርኒያ ለማረፍ አየርላንድ የመገኘት አስቂኝ ስህተቱ ዳግላስ ኮሪገን ቢተችም ልምድ ያለው አብራሪ ብሎም ክህሎት ያለው የአውሮፕላን መካኒክ ስለመሆኑም ይነገርለታል።
ከስህተቱ 11 አመታት አስቀድሞም አሜሪካዊው ቻርለስ ኤ. ሊንደርበርግ ለመጀመሪያ ጊዜ የአትላንቲክ ውቅያኖስን ያለማቋረጥ በርሮ አለም አቀፍ ዝነኛ ሲሆን ኮሪገን በሊንደርበርግ አውሮፕላን በመካኒክነት ይሰሩ ከነበሩ ባለሙያዎች አንዱ ነበር። የቴክሳስ ውልደት ላለው ኮሪገን ግን ይህ የታሪክ አካልነት በቂ አልሆነለትም።
ኮሪገን በ1930 ዓ.ም. የ1921 ዓ.ም. ከርቲስ ሮቢን የተሰኘች አውሮፕላንን ከወደቀችበት ገዛ። እንደገና ጠገናት። ረዥም ርቀት ለመጓዝ የሚያስችል ማስተካከያም አደረገላት። ይህችንው ባለ አንድ ሞተር አውሮፕላንን ከካሊፎርኒያ ወደ ኒው ዮርክ ያለማቋረጥ አበረራት።
ከወደቀችበት አንስቶ በጠገናት አውሮፕላን መብረር በመቻሉ ትኩረትን መሳብ ችሏል።
ኒውዮርክ መድረስ ከቻለ በኋላ ወዲያው በጠገናት አውሮፕላን ያትላንቲክ ውቅያኖስን የማቋረጥ እቅድን አወጣ።
ግና የበረራ ባለስልጣናት ራስን የማጥፋት የበረራ እቅድ ነው ሲሉ እቅዱን ከለከሉት። በምትኩ ወደ መጣበት ካሊፎርኒያ እንዲመለስ ፈቀዱለት።
ከኒው ዮርክ ወደ ካሊፎርኒያ አቅጣጫ የበረራ ጉዞውን ጀመረ። ግና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋል የበረራ አቅጣጫው ባልተጠበቀ መንገድ ዞረ። የበረራ ባለስልጣናት ራስን የማጥፋት ዕቅድ ወዳሉት የበረራ አቅጣጫ።
ኮሪገን የአትላንቲክ ውቅያኖስ ሰማይን ሰንጥቆ ለአንድ ቀን በረረ። ከ84 አመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት 28 ሰዓታትን በበረራ ላይ ካሳለፈ በኋላ በአየርላንድ ደብሊን አውሮፕላኑን አሳረፈ።
አውሮፕላኑን ካሳረፈ በኋላ የጠየቀው ጥያቄም ‘’ከኒው ዮርክ ገና ገባሁ፤ የት ነው ያለሁት?’’ የሚል ነበር። በ5 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት ሊያርፍ ካሰበበት ያረፈው ኮሪገን በጊዜው በደመና ሳቢያ አቅጣጫውን ስለመሳቱ እና ኮምፓሱ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖበት እንደነበር ተናግሯል።
ኮሪገን በዚሁ ክስተት ሳቢያ የማብረር ፍቃዱን ቢነጠቅም በሁለቱም የአትላንቲክ ጫፎች የጨዋታ ምንጭ በመሆን እውቅ ሆኗል። የተሳሳታው መንገድ ኮሪገን ‘’Wrong Way Corrigan’’ የሚለው ስያሜም መታወቂያው ሆኗል። በጊዜ ኮሪገን እና አውሮፕላኗም ያቋረጡትን አትላንቲክን በመርከብ ተመልሰውበታል።
ልምድ ያለው አብራሪ የነበረው ኮሪገን በዚህ አትላንቲክን ባቋረጠበት በረራው ቢተችበትም ይዟት የነበረችው አውሮፕላን ሬድዮ ያልነበራት ብሎም ኮምፓሷ የ20 ዓመት እድሜ ያለው ነበር። የተገጣጠመችውም በራሱ እጆች ነበር።
ከተሳሳተ የበረራ አቅጣጫው ባሻገር ከዚያ ዓይነት በረራ በመትረፉም ጭምር የግርምት ምንጭ ሆኗል። በጊዜው መንገዱን መሳቱን ያወቀው ከ10 ሰዓታት ጉዞ በኋላ ስለመሆኑም ተናግሮ ነበር። ለመመለስም ረፍዷል። 18 ሰአታት ጨምሮበት 28 ሰአታት ከተጓዘ በኋላም በሰላም አርፎ ወደ አሜሪካ በመርከብ ተመልሷል።
በአብርሃም በለጠ
2022-07-18
