ከ42 ዓመታት በፊት ወደተከናወነው ኦሎምፒክ እንወስዳችኋለን። በዚህ በሶቭየት ህብረት በሞስኮ በተከናወነው ኦሎምፒክ ምሩጽ ይፍጠር ደምቆበታል። 60 ሀገራትም አንሳተፍም ያሉበት ኦሎምፒክ ነው። ይሄው ኦሎምፒክ ጅማሬው በዛሬዋ እለት በ1972 ዓ.ም. ነበር።
ጊዜው 1972 ዓ.ም. ነው። 22ተኛው ኦሎምፒክ እንዲካሄድ ተፈልጓል። ለማስተናገድም ሁለት ከተሞች ተመርጠዋል። ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ሎስ አንጀለስ እና ከሶቭየት ህብረት ሞስኮ። በ75ተኛው የአለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ስብሰባ ሞስኮ ለአስተናጋጅነት በ39 ድምጽ ተመራጭ ሆነች።
በሌላ በኩል በጊዜው የፖለቲካ ትኩሳት አለ። በ1971 ዓ.ም. ሶቭየት ህብረት ደቡባዊ ጎረቤቷን አፍጋኒስታንን ወራለች የሚሉ ወቀሳዎች በርክተዋል። ኋላም ይሄው የሶቭየት ህብረት ጥቃት አፍጋኒስታንን ለርስ በርስ ጦርነት ዳርጓታል። ለሶቭየት ህብረት መፍረክረክም አንዱ ምክንያት ሆኗል።
ይሄው የሶቭየት እና አፍጋኒስታን ጦርነት በሞስኮ ሊካሄድ ከተወሰነው ኦሎምፒክ ላይ የራሱን ተጽዕኖ ማስደሩ አልቀረም። የፖለቲካ ፍላጎት በኦሎምፒክ መድረኩ ላይ ተንጸባረቀ። በታሪክ ከምዕራባውያኑ ረድፍ ወጥቶ በምስራቁ ረድፍ በሶሽያሊስት ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነው ይሄው ኦሎምፒክ ትልቁን አድማ አስተናገደ።
በኦሎምፒክ ታሪክ ውስጥ ትልቁን አድማ በማስተናገድም ቀዳሚው ነው። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር አድማውን በመጥራት ተቀዳሚው ሆኑ። 60 ሀገራት የአሜሪካን ጥሪ በመከተል በሞስኮው ኦሎምፒክ ላለመታደም አደሙ።
ያም ሆኖ ግን 81 ሀገራት ተገኝተውበታል። 5000 አትሌቶችም ተሳታፊ ሆነውበታል። ሶቭየትን አፍጋኒስታንን ወረሻል ይሉት ተቃውሞዎች ቀጥለዋል። በመክፈቻ ስነ ስርዓቱም ብዙ ሀገራት አልተገኙም። በዚህ ከ42 ዓመታት በፊት በተካሄደው ኦሎምፒክ ሀገራችን ኢትዮጵያም አትሌቶቿን ይዛ ተገኝታበታለች። 25 ወንድ እና 2 ሴት የሀገራችን አትሌቶች ተሳትፈውበታል።
በአድማው የኦሎምፒክ ውድድሩ መንፈስ ተጽእኖ አድሮበታል። በጥቅሉ የሶቭየት ህብረት የኦሎምፒክ ቡድን 80 የወርቅ ሜዳሊያዎችን፣ በጥቅሉ 195 ሜዳሊያዎችን ሰብስቧል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሞስኮ ኦሎምፒክ 2 ሴት አትሌቶችን ፋንታዬ ሲራክ እና አምሳለ ወ/ገብርኤል ያሳተፈችና ቀደም ብላ ከተሳተፈችባቸው ሁሉ የተሻለ ሜዳልያ ያስመዘገበችበት ኦሎምፒክም ነበር፡፡
በዚህ ውድድር ሀገራችን ኢትዮጵያ በውድድሩ የመጨረሻ ሰአት ላይ ፍጥነቱን በመጨመር ለተፎካካሪዎቹ ፈተና በነበረው በማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠር የ5 ሺህ ብሎም የ10 ሺህ ሜትር ርቀት ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በእጇ አስገብታለች። በዚህ ምሩጽ ይፍጠር በአንድ ኦሎምፒክ በሁለት ውድድሮች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ የማይረሳ ገድል ጽፏል።
በሞስኮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በ5,000ሜ እና 10,000 ሜትር በሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሁለት የወርቅ፣ በመሃመድ ከድር በ10,000 ሜትር እና በሻምበል እሸቱ ቱራ በ3,000 ሜትር መሰናክል በተገኙ 2 የነሃስ፣ በድምሩ በ4 ሜዳልያዎች በኦሎምፒኩ ላይ ከተሳተፉ የዓለም ሃገራት በአትሌቲክስ 6ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡
በዚህ የብዙ ሀገራትን አድማ ባስተናገደው የኦሎምፒክ ጨዋታ ጎን ለጎን ሀገራት በኦሎምፒክ አርማ ስር ከሞስኮ ውጭ ውድድሮችንም አካሂደውበታል። በዚህ የኦሎምፒክ ጨዋታም ሶቭየት ህብረት ከምስራቅ ጀርመን ጋር ተደምሮ ግማሽ የሚሆን የውድድሩ ሚዳሊያ የርሷ ሆኗል።
በአብርሃም በለጠ
2022-07-19
