ሀገሬ ቲቪ

ሩሲያ የዩክሬንን ወደቦች ልትከፍት ትችላለች ተባለ

ምዕራባዊያንም በሩሲያ ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀቦችን ቢጥሉም በዩክሬን ላይ የጀመረችውን ጦርነት ከማቆም ይልቅ አጠናክራ ቀጥላለች። ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰም ይገኛል፡፡

ለዩክሬን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመለገስ ሩሲያን ለማሸነፍ የታቀደው ውጥን ፍሬ አለማፍራቱ እና ተጨማሪ የዩክሬን ከተሞች በሩሲያ እጅ ስር መውደቃቸው ምዕራባዊያኑን አሳስቧል፡፡

ሩሲያን በመቅጣት ዩክሬንን ማትረፍ በሚል ተይዞ የነበረው የምዕራባዊያን እቅድም ውጤት እያመጣ ባለመሆኑ ዩክሬን እና ሩሲያ አለመግባባታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ማሳሰብ ከጀመሩ ስንብተዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ከቱርክና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር የሩሲያ ወረራ ከተጀመረበት ከየካቲት 17/2014 ዓ.ም. አንስቶ በዩክሬን ጎተራዎች ውስጥ የተከማቸውን በሚሊዮን ቶኖቾ የሚገመት እህል ኤክስፖርት ለማድረግ አጠቃላይ ስምምነት መኖሩን ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል፡፡

የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አሁን በሩሲያ ላይ የተጣሉትን ማዕቀቦች አፈፃፀም ለማጠናከርና እንዲሁም በሩሲያ ወርቅ ሽያጭ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንዲጣል ከማቀድ ጋር ለዩክሬን ወታደራዊና ተጨማሪ እገዛ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ብራስልስ ተቀምጠዋል።

ሩሲያ ኦዴሳንና ሌሎችም የዩክሬን ወደቦችን ለመክፈት በዚህ ሣምንት ትስማማለች ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ሰኞ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

እርምጃው ብዙ ሀገሮች ውስጥ ለተፈጠረው የምግብ እጥረት መፍትኄ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፤ ቦሬል ብራስልስ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሩሲያ የዩክሬንን ወደቦች ልትከፍት እንደምትችል ተስፋ አለኝ ብለዋል።

“ሩሲያ የዩክሬን እህል እንዲወጣ መፍቀድ አለባት ወይም ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ሩሲያ ስለ ሰው ልጆች ምንም ደንታ ሳይሰጣት ምግብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመችበት ነው ብሎ መናገር ይኖርበታል ፤ይህ የዲፕሎማሲ ጨዋታ አይደለም፤ለብዙ ሰዎች የህይወትና የሞት ጉዳይ ነው”

ሩሲያ አውሮፓዊያን በሩሲያ ጋዝ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት በመጠቀም በአውሮፓ ኅብረት ሀገሮች አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እየተጠቀመችበት ነው ያሉት ቦሬል ይሁን እንጂ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ሊገጥም የሚችለውን ማናቸውንም ችግር ለመቋቋም ዕቅድ በማውጣት እየተዘጋጁ መሆናቸውንና ዩክሬንን መደገፋቸውን እንደማያቆሙ ገልፀዋል።

ቦሬል አክለውም የአውሮፓ ኅብረት ሀገሮች ሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የሚያደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም ትዕግሥትና ፅናት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

የአውሮፓ ሚኒስትሮች ዩክሬን ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ መረጃዎችን ከዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሚትሮ ኩሌባ እያገኙ መሆናቸውን ቦሬል አስታውቀዋል።

ዩክሬን ውስጥ ሩሲያ ስሎቭያንስክና ኻርኪቭን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎችን በከባድ መሣሪያ እየደበደበች መሆኑን የዩክሬን ጦር ያውጣው መረጃ ያሳያል።

በዚህኛው በኩል የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሴፕ ታይፕ ኤርዶጋን እና የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ ጋር ለመወያየት ቴህራን ውስጥ ናቸው።

ፑቲን እና የቱርኩ ኤርዶሃን በጥቁር ባሕር በኩል የዩክሬንን የእህል ምርት ወደ ውጭ እንዲውጣ ለማገዝ በሚል ስምምነት ላይ እንደተወያዩም ተሰምቷል።

የፖለቲካ ተነታኞች እንደሚሉት ከሆን ምን አልባትም ሩሲያ ከቴህራን ቆይታዋ በኋላ የዩክሬንን የእህል ምርት እንዲወጣ ትፈቅድ ይሆን የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ነው።

በፍሬሕይወት ታደሰ
2022-07-19