ሀገሬ ቲቪ

ዕለቱን ከታሪክ-የመጀመሪያዎቹ ጨረቃ ላይ ያረፉ እግሮች

ዛሬ ላይ የሰው ልጅ አጽናፈ ዓለምን የመመርመር ፍላጎቱ ከመሬት በ1.5 ሚሊዮን ኪ.ሜ. ርቀት ቴሌስኮፕ አስቀምጦ የጥልቁን የህዋ ምስል እስከመቀበል አድርሶታል።

በዛሬዋ ዕለት ከ56 ዓመታት በፊት ነበር የሰው ልጅ በምሽት በዓይኖቹ ብቻ ይመለከታት የነበረችው ጨረቃ ላይ የሰው ልጅ እግሮች ያረፉት። የጠፈርተኛው ኒል አርምስትሮንግ ድምጽን ከጨረቃ ላይ ከቢሊዮን የሚልቁ ሰዎች በየቤታቸው ሰምተውታል።

በጠፈር ምርምሩ ዘርፍ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሶቭየት ህብረት ፉክክር ላይ ናቸው። ማን ጨረቃ ላይ ቀድሞ ጠፈርተኞቹን ይልክ ይሆን? የሚለው ደግሞ የፉክክሩ አካል ነው።

ሶቭየት ህብረት ስፑትኒክ 1 የተሰኘችውን የመጀመሪያዋን ሰው ሰራሽ ሳተላይት ወደ ጠፈር በመላክ አሜሪካንን ቀድማለች። በጠፈርተኛው ዩሪ ጋጋሪን በኩልም በቮስቶክ 1 መንኮራኩር መሬትን በመዞርም ቀዳሚ ሆናለች።

የጠፈር ፉክክሩ በጦፈበት በዚያ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ጠፈርተኛን ወደ ጨረቃ የመላክ የአሜሪካን ጥረት በተመለከተ ታዋቂ ንግግራቸውን በ1953 ዓ.ም. አደረጉ።

በጊዜው አሜሪካ እና ሶቭየት ህብረት የጦፈ የጠፈር ምርምር ፉክክር እና የቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ናቸው። ከኬኒዲ ንግግር 4 አመታት በኋላ ከአምስት አመታት የአሜሪካ የጠፈር ተቋም ናሳ ምርምር በኋላ በ1956 ዓ.ም. ሰው አልባ የአፖሎ ተልዕኮ ሙከራ ተከናወነ። ጉዞው ሰውን ወደ ጨረቃ ወደ መላክ ነው።

በቀጣዩ አመት አንድ አሳዛኝ ሁነት ተከሰተ። በፍሎሪዳ በኬኒዲ የጠፈር ማዕከል ሰው የያዘች የአፖሎ መንኮራኩር እና የሳተርን ሮኬትን ለማስወንጨፍ በተካሄደው ሙከራ እሳት ተነስቶ ሶስት ጠፈርተኞች ለሞት ተዳርገዋል።

ከዚህ አደጋ በኋላም ቢሆን ናሳ ስራውን ቀጠለ። በቀጣዩ አመትም የአፖሎ 7 ተልዕኮ ሰውን ይዞ በመሬት ዙሪያ በመሽከከርከር ለጨረቃ ጉዞ የሚያስፈልጉ አጠቃላይ የጉዞ ስርዓት ሙከራዎችን በተሳካ ሁኔታ ምድረግ ተችሏል።

ከተከታታይ ሙከራዎች በኋላም በ1961 ዓ.ም. በአፖሎ 11 ተልዕኮ ወደ ጨረቃ ሰውን የመላክ ዕቅድን ማሳካት ተችሏል።

አፖሎ 11 መንኮራኩር ከኪኔዲ የጠፈር ተቋም እንድትነሳ ተደረገ። ጠፈርተኞቹን ኒል አርምስትሮንግን፣ ኤድዊን አልዲን ጄአርን እና ሚካኤል ኮሊንስን ይዛለች። የ38 አመቱ አርምስትሮንግ የተልዕኮው መሪ ነበር።

ጠፈርተኞቹ ለ76 ሰዓታት ከ386 ሺህ ኪ.ሜ. በላይ ከተጓዙ በኋላ አፖሎ 11 የጨረቃ ምህዋር ደረሰች። በዛሬዋ ዕለት ከ61 ዓመታት በፊት ጠዋት ላይ አርምስትሮንግ እና አልድሪን ከዋናዋ ማዘዣ መንኮራኩር ኮሊንስን በመተው ኤግል ተብላ በምትጠራው ወደ ጨረቃ መውረጃ ወረዱ።

ከሁለት ሰዓታት በኋላ ኤግል በጨረቃ ስፍራ ላይ ማረፍ ጀመረች። የጨረቃን ስፍራ እንደረገጠችም አርምስትሮንግ ሆስቲን ቴክሳስ ለሚገኘው የተልዕኮው ተቆጣጣሪ በሬድዮ ‘’ኤግል አርፋለች’’ ሲል መልዕክቱን አስተላለፈ።

ቀጣዩ ሁነት በተገጠመ ካሜራ ለዓለም ህዝብ በሲግናል ይደርሳል። በ100 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሁነቱን በጉጉት ይከታተሉታል።

ኒል አርምስትሮንግ ወደ ጨረቃ መውረድ ጀመረ። የግራ እግሩን አስቀድሞ ከጨረቃ ላይ አሳረፈ። የሰው እግሮች ጨረቃን ረገጡ። አርምስትሮንግ በጨረቃ ላይ ሲራመድ ታዬ። አልድሪን ተከተለው። የአሜሪካ ሰንደቅንም ከጨረቃ ላይ ተጅከሉ። የሰው ልጅ የጠፈር ምርምር ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታሪክም ሆነ።

ሁለቱ ጠፈርተኞች የጨረቃ ላይ ቆይታቸውን ካደረጉ በኋላ በዚያችው ዕለት ሌሊት ወደ ማዘዣ መንኮራኩሯ ተመለሱ። አፖሎ 11 ወደ መሬት ያደረገችውን መመለስም በተሳካ ሁኔታ አድርጋ በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ማረፍ ችላለች።

በአብርሃም በለጠ
2022-07-20