ሀገሬ ቲቪ

ለገበያ የቀረበ ፍየል አልሸጥም ሲል አለቀሰ

ሰው አብሮ ከኖረው አይደለም ለደቂቃ ጥሩ ግዜን ካሳለፈው ሰው ጋር ሲለያይ ሆድመባሱ አየርም።የመለየት ክብደቱን የደረሰበት ያውቀዋል። ይህ በሰዎች ዓለም የምናውቀ ሰው ነው።

እንዲህ ያሉ ስሜቶች በርግጥ በእንስሳቱም ዓለም ውስጥ ሲገለፁ ሰምተንም አይተንም ይሆናል። በተለይ ከሰው ልጆች ጋር የበለጠ ቁርኝት ያላቸው ውሻ እና ድመቶች ለዚህ ስሜት ይቀርባሉ።

እኛም ከሰሞኑ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ቀልብን ያዝ ያደረገ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስልን ብንመለከት ልናጋራችሁ ወደድን። ባሳለፍነው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ለገበያ የቀረበ አንድ ፍየል ባለቤቱን በእንባ ሲሰናበት የሚያሳይ።

ነገሩ የበርካቶችን አንጀት የበላ ነው። ፍየሉ ከባለቤቱ ትከሻላይ ላይ አንገቱን አስደግፎ እሪታውን አስነክቶታል። ተንቀሳቃሽ ምስሉ ዘግይቶ አደባባይ ቢወጣም ነገሩ ግን ለበርካቶች ግርምን ያጫረ ነበር።

የፍየሉ ባለቤት ከገዢው ጋር በሚስማማበት ሰዓት ፍየሉ እሪታውን ማስነካት እንደጀመረ ምስሉን ወደ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ብቅ ያደረጉት ሰዎች አስነብበዋል።

በገበያው የታደመው ሻጭ፣ ገዚ እና ሌላውም የፍየሉን ለቅሶ ተከትሎ አብሮ ሲያለቅስም ነበር። ባለቤቱም ቢሆን ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት አብሮት ሲያለቅስም ተስተውሏል። ታዲያ ይህ ሁሉ ፍየሉን ከመሸጥ አላደነውም።

ፍየሎች ልክ እንደሰው የርህራሄ ልብ ያላቸው እንደሆኑ በሮያል ሶሳይቲ ላይ የወጣ ጥናት ያመለክታል። እንደ ሰው ማለታችን በርህራሄ ለታደሉት ማለታችን ነው።

የሰውን ስሜታዊ አገላለጾች መረዳት ከሚችሉ ፍጥረታት መካከል ፍየሎች አንደኞቹ ናቸው ይላል በ2010 ዓ.ም የተደረገው ጥናቱ አመላክቷል። 35 ፍየሎች በዚህ ጥናት ላይ መሳተፋቸውን ኤን.ዲ ቲቪ በድረ ገፁ አስነብቧል።

መቼም የሰው ልጅ ልብ ከድንጋይ በላይ በደነደነበት በዚህ ግዜ እንዲህ ካሉ እንስሳት ምን እንማር ይሆን።

በሳምሶን ገድሉ
2022-07-20