የአስዋን ግድብ በአለም ላይ ትልቅ ከሚባሉ ግድቦች አንዱ ነው። ይሄው በአፍሪካ በግብጽ በናይል ወንዝ ላይ የተገነባው የአስውን ግድብ የተጠናቀቀው በዛሬዋ እለት በ1963 ዓ.ም. ነበር። የ11 አመታት የግንባታ ጊዜን ፈጅቷል።
የ111 ሜትር ከፍታ እና የ3218 ሜትር ርዝመት አለው። በአፍሪካ በትልቅነቱ የሶስተኛ ደረጃን የያዘ ግድብ ነው። የኛው የህዳሴ ግድብ የአንደኝነቱን ስፍራ ይይዛል።
በ1940ዎቹ የግብጽ ፕሬዝዳንት ጋማል አብደል ናስር በናይል ወንዝ ላይ ትልቅ ግድብ የመስራት ዕቅድን አሳወቁ። ይሄው ትልቅ ግድብ የናይል ወንዝ የጎርፍ አደጋን ያስቀራል፤ ለሁሉም የግብጽ ዳርቻዎች የኤለክትሪክ ኃይልን ያቀርባል ተባለለት። ጋማል አብደል ናስር የአሜሪካ እና የእንግሊዝ የገንዘብ ተቋማትን ድጋፍ አሸነፉ።
ከታቀደው የአስዋን ሃይ ዳም አስቀድሞ በ19ነኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ግብጽን ታስተዳድር በነበረችው እንግሊዝ የአስዋን ሎው ግድብ ተገንብቶ ነበር። የዚህን ግድብ አቅም ለማሳደግ ግን የትልቁ ግድብ መገንባት ነገር በግብጽ መንግስት የጊዜው ትልቅ ዕቅድ ሆኗል።
ግና ደግሞ ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ የነበሩት አሜሪካ እና እንግሊዝ ግብጽ ከሶቭየት ህብረት ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ተስማማታለች በሚል ለግድቡ ሊያደርጉ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍን ሰረዙ።
ናስር የስዊዝ ካናል ገቢ ለታሰበው ትልቅ ግድብ የገንዘብ ምንጭ እንዲሆን በማሰብ በእንግሊዝ እና አሜሪካ ቁጥጥር ስር የነበረውን ስዊዝ ካናልን ነጥቀው የግብጽ ነው አሉ። ይሄው ክስተት የስዊዝ ቀውስን አስከተለ።
በ1948 ዓ.ም. እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና እስራኤል በህብረት ግብጽን አጠቁ። የስዊዝ ካናልንም ከግብጽ ወሰዱ። ኋላም ሶቭየት ህብረት፣ አሜሪካ እና የተባበሩት መንግስታት በጋራ ሶስቱን ሀገራት አስቆሙ። ስዊዝ ካናልም ለግብጽ ተመለሰ።
በ1952 ዓ.ም. የአስዋን ግድብ ስራ ተጀመረ። ይሄው ግድብ የተነደፈው የሶቭየት መሰረት ብላው የውሃ ፕሮጀክት ተቋም ነበር። የግድቡ ስራ እንዲጀመር ያስቻሉት ግን የሶቭየት ህብረት ብድር እና ከስዊዝ ካናል የተገኘው ገቢ ነበሩ። 43.5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መሬት እና አለት ጥቅም ላይ ውሏል።
ሶቭየት ለግድቡ ግንባታ ብድር ከመስጠቷ በተጨማሪ ባለሙያዎቿንና ማሽኖቿን ልካለች። ንድፉም የተሰራው በሶቭየት ተቋም ከተወሰኑ የግብጽ ኢንጂነሮች ጋር በትብብር ነበር። በግድቡ ስራ ላይ 25 ሺህ ግብጻውያን ኢንጂነሮች እና ሰራተኞችም ተሳታፊ ሆነዋል።
አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጭ ያስወጣው የግብጽ ትልቁ ግድብ አስዋን በ1962 ዓ.ም. ስራው ተጠናቋል። ግን ደግሞ መጠናቀቁን እንዲሰራ የለፉለት ናስር በህይወት አላዩትም።
ለክብራቸው ሲባልም የግድቡ ትልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ናስር ሀይቅ ተብሎ ተሰይሞላቸዋል። የዚሁ ሀይቅ መፈጠርም 90 ሺህ የግብጽ ገበሬዎችን እና የሱዳን አርብቶ አደሮችን አፈናቅሏል። አቡ ሲምበል የተሰኘው የግብጽ ጥንታዊ ቤተ መቅደስ ከቦታው እንዲዘዋወርም አስገድዷል።
የአስዋን ግድብ የናይል ወንዝን ጎርፍ በማቆም 40 ሺህ ሄክታር የሚሆን በርሃማ ስፍራ እንዲለማ ማድረግ ችሏል። በተጨማሪም 324 ሺህ የሚጠጋ ሄክታር መሬት የተለያዩ ሰብሎችን ማምረት እንዲችል ማድረግ ችሏል።
በሶቭየት የተገነቡ 12 የግድቡ ተርባይኖች 10 ቢሊዮን ኪሎ ዋት አወርስ ኃይልን በአመት ያመነጫሉ። ይሄው ትልቅ ግድብ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የግብጽ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አወንታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። የግብጽ መንደሮችንም ከዘመኑ ስልጣኔ አስተዋውቋል።
44,300,000 ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ግድቡ የአሳ ማምረት ኢንዱስትሪንም አሳድጓል።
በናይል ወንዝ ላይ የተገነባው የአስዋን ግድብ የሌሶቶው ካስቴ አርች ግድብ እስኪጠናቀቅ የአንደኝነት ደረጃውን ይዞ ነበር። የኛው የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ የአንደኝነት ደረጃውን ሲይዝ ደግሞ ደግሞ የሶስተኝነት ደረጃውን ይዟል።
በአብርሃም በለጠ
2022-07-21
