በዓለማችን 369 ሚሊዮን ዘራፊዎች እንዳሉ ይታመናል።
በዓለማችን ከሚፈፀሙ ወንጀሎች 52 በመቶ የሚሆኑት የዝርፊያ ወንጀሎች ናቸው።
እንደ ዘግሎባል ኢኮኖሚ ጥናት በ100 ሺህ ቤቶች ውስጥ 105 ዝርፍያ ይፈፀምባቸዋል።
ታዲያ እነዚህን ሁሉ ወንጀሎች ፈልፍሎ ዘራፊዎቹን ለህግ ማቅረብ ደግሞ የፖሊሶች ሌላኛው ፈተና ነው።
ያጠፋ ሊቀጣ ይገባዋል እና የቻሉትን መንገዶች ሁሉ ተጠቅመው ወንጀለኛውን ህግ ፊት ይዘውት ይቆማሉ።
ከወደ ቻይና አንድ ወንጀለኛ ለመያዝ እራሳቸውን መስዋዕት ስላደረጉ ቢንቢዎች ብንሰማ ልናወራችሁ ወደድን።
ግለሰቡን ፖሊስ በሌሎች ሦስት የዝርፊያ ወንጀሎች እፈልገው ነበር ብሏል።
የእነዚህ ቢብቢዎች ተጋድሎ ይህንን ይመስላል።
ሌባ ሆዬ ወደ ቤቱ ሰተት ብሎ ይገባል ወርቅን ጨምሮ በርካታ ጌጣጌጦችን ሰብስቦ ወደ ቋቱ ይከታል።
በዚህ ብቻ መቼ አበቃና ይላሉ ፖሊሶች።
ወደ ኩሽና ጎራ ብሎም ከካቢኔቱ ውስጥ ኑድል አውጥቶ በእንቁላል ክሽን አድርጎ የዕለት ርሀቡን ያስታግሳል።
ይህም አላጠገበውም በቤቱ ውስጥ የቀረችዋን ምሽት ለማሳለፍ ጋደም ይላል።
ታዲያ ጋድም ባለበት ሁለት ቢምቢዎች እረፍትን ይነሱታል። በቢቢዎች የተማረረው ሌባም አሳዶ በግድግዳው ላይ በእጁ ይለጥፋቸዋል።
በጊዜው በቤት ውስጥ ያልነበሩት ባለቤቶች ቤታቸው ሲደርሱ ባዩት ነገር ቆሌያቸው ይገፈፋል።
ፖሊስ በቦታው ተገኝቶ ምርመራ ሲያደርግ ታዲያ ሰው ባልነበረበት በዚያ ምሽት በግድግዳ ላይ ደማቸው የፈሰሰውን ቢንቢዎች ይመለከታል።
ከሞቱት ቢንቢዎች የዲኤን ኤ ናሙና በመውሰድም ምርመራውን ይጀምራል።
ከቤቱ በርካታ ውድ ጌጣጌጦችን የዘረፈውንም ወንጀለኛ ቢንቢዎቹ በተገኝ የምርምራ ወጤት ከ19 ቀናት በኋላ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።
ባለውለታዎቹ ቢንቢዎች በህይወት መቆየት ባይሆንላቸው ዘራፊውን ከህግ ፊት ለማቅረብ ግን የማይናቅ ሚናን ተጫውተዋል እየተባለላቸው ይገኛል።
ዘገባውን ግሎባል ኒውስ አጋርቶናል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-07-22
