ሀገሬ ቲቪ

የቀዝቃዛው ጦርነት መሪዎች ኒውክሌር መሳሪያን የመገደብ ስምምነት

አሜሪካ እና ሶቭየት ህብረት አንዱ በሌላው ላይ የበላይ ለመሆን የሚያደርጉት ፉከከር በጦር መሳሪያ የመደርጀትም ጭምር ነበር። የኒውክሌር ሚሳኤል ማምረት ደግሞ አንዱ ነው።

የሶቭየት ህብረት የመጨረሻው መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ የኒውክሌር የጦር መሳሪያን የሚከለክል ስምምነትን ከአሜሪካው መሪ ሮናልድ ሬገን ጋር ማድረግ ችለዋል።

በዛሬዋ ዕለት ነበር በ1979 ዓ.ም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎች ላይ የእገዳ ስምምነትን ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹት።

የሚካኤል ጎርባቾቭ የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እገዳ የማድረግ ድርድር ለማካሄድ ፈቃደኛ መሆን በጊዜው እንደታምር የታዬ ሁነት ነበር፡፡ ይሄው የጎርባቾቭ ውሳኔ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ላደረጉት የመካከለኛ ርቀት የኒውክሌር ሃይሎች (INF) ስምምነት መንገድ ጠርጓል።

ጎርባቾቭ ገና ወደ ስልጣን ሲመጡ ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ጋር እንደቀድሞ የሶሻሊስት እና ካፒታሊስት ሀገራት መሪዎች መነቋቆር ያልበረከተበት ግንኙነት የመመስረት ዝንባሌ ነበራቸው።

የአሜሪካ አቻቸው ሮናልድ ሬገን ደግሞ በተቃራኒው ጥብቅ ጸረ ኮሚዩኒስት አቋም ነበራቸው። መጀመሪያ ላይም የጎርባቾቭ ቅንነት የተደበቀ ተንኮል አለው በሚል አጥብቀው ጠርጥረዋል።

በ1978 ዓ.ም ከጎርባቾቭ ጋር ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ግን በብዙ ጉዳዮች ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመኑ። ከነዚህም መካከል የኃይል ፉክክር ምንጭ የሆነው የሀገራቱ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ላይ መስማማት አንዱ ነበር።

በተከታታይ ግንኙነቶች ጎርባቾቭ እና ሬገን የመካከለኛ ርቀት የኒውክሌር መሳሪያዎች ላይ መምከሩን ተያያዙት። ሶቭየት እና አሜሪካ በጦር መሳሪያ ክምችቱ ከዓለም ሀገራት ቀዳሚ ናቸው።

ለአንድ ዓመት የተጠጋ ተከታታይ ንግግር ጊዜ በኋላ ከአውሮፓ የጦር መሳሪያን መቀነስ የሚያስችል ስምምነት ለማድረግ ቢቃርቡም ድርድሮቹ ተስተጓጎሉ።

ጎርባቾቭ ሚሳኤሎችን መቀነሱ ከአሜሪካ የባላስቲክ ሚሳኤል ጥቃትን የመከላከል ምርምር ስታር ዋርስ እቅድ (Star Wars plan) መተው ጋር እንዲተባበር ፈልገው ነበር።ባለመተማመን መካሰሶች ሚሳኤሎችን የማገድ ንግግራቸው ተቋረጠ።

ነገር ግን ጎርባቾቭ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚሳኤልን ለመቀነስ ለመወያየት ፈቃደኛ መሆናቸውን በማሳወቅ ከ35 ዐመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት አለምን አስደመሙ። ቅድመ ሁኔታዎችን አስወግደው ለድርድሩ መንገድ ከፈቱ። ከሬገን ጋር እንደገና ለመገናኘትም ስምምነት አደረጉ።

የጎርባቾቭን አእምሮ የቀየሩ የተለያዩ ምክንያቶችም ይጠቀሳሉ። ሀገራቸው በጊዜው የኢኮኖሚ ችግሮች ገጥመዋታል። የሩስያን የወታደራዊ በጀት የመቀነስም ፍላጎት ነበራቸው። ከምእራባውያኑ ሀገራት ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የማጠናከር ፍላጎት አላቸው።

በመጨረሻም ጎርባቾቭ ከሬገን ጋር ወዳጅነት አትርፈዋል። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የኒውክሌር ሚሳኤልን የመገደብ ስምምነትን ለማድረግ ጎርባቾቭ በገለጹ በወራት ውስጥ በአሜሪካ ዋሽንግተን ጎርባቾቭ ከአሜሪካው መሪ ሬገን ጋር የኒውክሌር የጦር መሳሪያዎችን የመቀነስ ስምምነትን የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል ስምምነትን ተፈራረሙ።

ይሄው ስምምነት የምስራቁ እና የምእራቡ የቀዝቃዛው ጦርነት ኃይሎች ግንኙነትን መልክ የቀየረ ነበር።

በአብርሃም በለጠ
2022-07-22