ባንኮች አሁን ካሉበት ደረጃ በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ተጠቆመ።
ይህንን ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ይናገር ደሴ ናቸው። ገዢው በፀሐይ ባንክ የስራ ማስጀመሪያ የምረቃ በርሃግብር ላይ በተገኙበት ወቅት ነው ይህንን ያሉት።
በሀገሪቱ ካሉ ዘርፎች በርካታ የገበያ እድል እንዳለው የሚነገርለት የባንክ ዘርፉ የሚገባውን ያህል የህብረተሰብ ክፍል ማዳረስ እንዳልቻለ ይነገርለታል።
አዲስ እየተቋቋሙ ያሉ ባንኮችን ጨምሮ በባንኩ ዘርፍ ላይ ውድድሮች እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቁመው ባንኮቹ ለተሻለ ውድድር እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል።
“በሀገራችን ያሉት ባንኮች ከጥቂቶቹ በስተቀር ሌሎቹ በርካታ ስራዎች ይቀሯቸዋል። በርግጥ ከስረው የተዘጉ ባንኮች ባይኖሩም አሁን የውጪ ባንኮች ወደ ስራ ሲገቡ በደንብ መፎካከር ግን መቻል አለባቸው”
በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች ቁጥር 30 መድረሱን አንስተው የባንክ ዘርፉ አሁንም እድሎች እንዳሉት ጠቁመዋል።
“በሀገሪቱ ያለው ባንክን የማይጠቀም ህዝብ ቁጥር እጅግ በርካታ ነው። በሀገሪቱ ያሉትም ሆኑ አዲስ የሚቋቋሙ ባንኮች የገበያ ችግር የለባቸውም።”
ባሳለፍነው ቅዳሜ በይፋ ስራ የጀመረው ፀሐይ ባንክ በሀገሪቱ በባንክ ዘርፍ እና በባንክ ፈላጊ ህብረተሰብ መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደሚሰራ አስታውቋል።
በመክፈቻ መርሀግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፀሐይ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሬድ መስፍን ባንኩ ትኩረት አድርጎ በሚሰራባቸው መስኮች ላይ ይህንን ብለዋል።
“በተለይ በሀገሪቱ ባንኮች ትኩረት የተነፈገውን የስራ ፈጠራ እና አነስተኛ እና መካከለኛ አምራቾችን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን።”
በሁሉም ዘርፍ የባንክ አገልግሎትን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለመስጠት መዘጋጀቱን ያስታወቀው ባንኩ ይህንንም እውን ለማድረግ ያግዝ ዘንድ ዘመናዊ የባንክ አጋግሎት መስጫ ሶፍትዌርን ጨምሮ፤ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎችን እንዲሁም የኤቲኤም አገልግሎትን ጭምር በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-07-25
