ሀገሬ ቲቪ

ዕለቱን ከታሪክ - ደራርቱ የመጀመሪያ ወርቋን ያገኘችበት ኦሎምፒክ

የዛሬው ዕለቱን ከታሪክ ትኩረቱን የኦሎምፒክ ታሪክ ላይ ያደርጋል። ወደ 1984 ዓ.ም. የባርሴሎና ኦሎምፒክ ይመልሰናል። በዚህ ኦሎምፒክ ደራርቱ ቱሉ በ10ሺህ ሜትር ወርቅ አስመዝግባለች።

በዚህም የመጀመሪያዋ በኦሎምፒክ ወርቅ ያገኘች ኢትዮጵያዊት አፍሪካዊት ለመሆን በቅታለች። ይሄው ኦሎምፒክ የተጀመረው በዛሬዋ ዕለት ነበር።30 ዓመታትን መለስ እንላለን።

ታሪክ ወደ ስፔይን ባርሴሎና ይወስደናል። የ1984 ዓ.ም. የባርሴሎና ኦሎምፒክ ጅማሮን ዛሬ ላይ ሆኖ እናገኘዋለን።

ይሄው ኦሎምፒክ በጣም ስኬታማው ዘመናዊ ኦሎምፒክ ተደርጎ ይታሰባል። 169 ሀገራት ተሳትፈውበታል። 9 ሺህ 300 አትሌቶች ተወክለውበታል።

በ30 ዓመታት ቀደም ያሉ የኦሎምፒክ ታሪክ ውስጥ ምንም አይነት ያለመሳተፍ አድማ ያላስተናገደ ኦሎምፒክም ነው። ለዚህ ምክኛትም በምስራቁ እና ምዕራቡ ዓለም በጊዜው ተአምራዊ ፖለቲካዊ ለውጦች ተደርገዋል።

ይሄው ኦሎምፒክ የተካሄደው ሶቭየት ህብረት በተከፋፈለች በአመቱ መሆኑ ከሶቭየት የተነጠሉት ሀገራት እንደ ነጻ ሀገር በዚሁ ኦሎምፒክ ላይ ተሳትፈዋል።

ምስራቅ እና ምዕራብ ጀርመንም የበርሊንን ግንብ አፍርሰው ወደ አንድነት ተመልሰዋል። ከአፍሪካ ምድርም ቢሆን ደቡብ አፍሪካ በዘረኛ አፓርድ ፖሊሲዋ ሳቢያ ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ ተነስቶላት ተሳታፊ ሆናለች።

ይህ ሁሉ ተደምሮ የባርሴሎና ኦሎምፒክን የተሳካለት ኦሎምፒክ አድርገውታል። የተሳታፊ ሀገራት ቁጥርም ከፍተኛ ነው። 169 ሀገራት በተሳተፉበት በዚህ ኦሎምፒክ ከ9 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች እንዲሳተፉ ሆኗል።

በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከሃምሌ 18 እስከ ነሃሴ 03/1984 ዓ.ም. በስፔን ባርሴሎና በተካሄደው በዚሁ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃገራችን በአትሌቲክስ 9 ወንድ እና 6 ሴት አትሌቶች በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች፣ በማራቶን እና እርምጃን ጨምሮ ለመሳተፍ የተመረጡ አትሌቶች ይዛ ተገኝታለች።

አትሌቶቻችን በወቅቱ ዋና አሰልጣኝ በነበሩት በአሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ እና ረዳቶቻቸው አማካይነት ዝግጅታቸውን አከናውነው ወደ ውድድሩ ስፍራ ተጉዘዋል።

በዚህ የባርሴሎና ኦሎምፒክ ልክ በጣሊያን ሮም አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ አድርጎ ዓለምን እንዳስደመመ።

ፍልቅልቂቷ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በ10ሺህ ሜትር ውድድር ታሪክ ጽፋለች። በርግጥ በጊዜው ደራርቱ ከውድድሩ ቀናት አስቀዶ በጠና ታማ ነበር።

ለውድድሩ የደረሰችውም ከህክምና ርብርብ በኋላ ነው። የሴቶች የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ ትንቅንቅ ውስጥ ነች። አየሩ ሞቃት ነው። ደራርቱ ግን ውሃ እንኳን ስትጠጣ አትስተዋልም። ሁለት አፍሪካውያን ከፊት ቀድመዋል።

ደራርቱ ቱሉ ከደቡብ አፍሪካዋ ሯጭ ሄሊና ሜየር ኋላ ትወነጨፋለች። በሞቃታማው አየር ሁለቱ አፍሪካውያን ፊት እና ኋላ ሆነው ይሮጣሉ።

አንድ ዙር ብቻ ቀረ። ድንገት ደራርቱ ከደቡብ አፍሪካዋ ሄሊና ሜየር መሪነቱን ተቀበለች። አንደኛ ሆናም አጠናቀቀች። የመጀመሪያዋ በኦሎምፒክ ወርቅ ያሸነፈች ጥቁር አፍሪካዊት ሴት ለመባል በቃች።

የኢትዮጵያንም ሰንደቅ ከፍ አደረገች። የደራርቱ ድል ለአፍሪካያን ትልቅ ድል ከመሆኑ በተጨማሪ የአሸናፊነት ግምቱ ውስጥ አልተካተተችም ነበር።

የደቡብ አፍሪካዋ ሄሊና ሜየር ከርሷ ቀጥሎም የአሜሪካ እና አየርላንድ አትሌቶች ነበሩ ቅድመ ግምት የተሰጣቸው። ፍልቅልቂቷ ደራርቱ ግን ከቅድመ ግምትም በላይ ሆነች። የመጀመሪያነትን ታሪክ ጻፈች።

በዚሁ ኦሎምፒክ ፊጣ ባይሳ በ5000 ሜትር የነሃስ ሜዳልያ አስመዝግቧል። ሌላው ኢትዮጵያዊው ሀዲስ አበበ ደግሞበ10000 ሜትር ነሀስ ሜዳልያን ማስመዝገብ ችሏል።

በደራርቱ በተገኘው አንድ ወርቅ እና በፊጣና ሀዲስ ባስመዘገቡት ሁለት የነሃስ ሜዳልያዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ በኦሎሚኩ በአትሌቲክስ ከአፍሪካ 3ኛ ከዓለም 12ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

በአብርሃም በለጠ
2022-07-25