ኤስያን ከአውሮፓ በባህር መስመር ለማገናኘት አፍሪካን መዞር የግድ ነበር።
የስዊዝ ካናል(ቦይ) መከፈት ግን ረዥሙን ርቀት በማሳጠር የዓለም የንግድ ሁኔታ ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳድራል።
ለግብጽ ቅርበት ቢኖረውም የስዊዝ ቦይ ለ87 ዓመታት በበላይነት ተቆጣጥረውት የነበሩት እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ነበሩ። ኋላም በ1948 ዓ.ም. ግብጽ ከሁለቱ ሀገራት ነጥቃ በዛሬው ዕለት የኔ ነው ብላለች።
ይሄው ክስተትም የስዊዝ ቦይ የግብጽ እንዲሆን መንገድ ጠርጓል።
ኤስያን ከአውሮፓ በመርከብ ጉዞ ለማገናኘት ረዥሙን መንገድ አፍሪካን የሚዞረውን የባህር መስመር መከተል የግድ ነበር፡፡ ከህንድ ውቅያኖስ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር በባህር ለመጓዝ በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል መዞር አማራጭ ያልነበረው መንገድ ነበር።
የኤስያ አውሮፓ ረዥም የንግድ የባህር መስመርን ለማሳጠር በቀይ ባህር እና በሜዲትራኒያን መካከል ያለውን የስዊዝ የባህር ሰርጥ የመናድ ሀሳብ ነበር። ሰው ሰራሽ የባህር መስመር የመዘርጋት ሀሳብ ነው።
ሁለቱን የውሃ አካላት የማገናኘቱ ሃሳብ ወደ 1920ዎቹ መለስ ይላል። ለዚህም ፈረንሳዊው አሳሽ እና ኢንጂነር ሊናንት ዲ ቤልፎንድስ ባደረገው ዳሰሳ ሁለቱ ባህሮች ተመሳሳይ ከፍታ ያላቸው መሆኑን መጠቆሙ ሰው ሰራሽ መስመሩን ለመዘርጋት ቀላል እንደሚያደርገው ግንዛቤ ውስጥ ገብቷል።
በ1840ዎቹ ግብጽን ያስተዳድር የነበረው የኦቶማን ኢምፓየር መሪ ከዲቭ ሰኢድ ፓሻ ለፈረንሳዩ ዲፕሎማት ፈርዲናንድ ዲ ሊሴፕስ መስመሩን የሚዘረጋ ድርጂት እንዲያቋቁም ፈቅዷል።
ይሄው ድርጂትም ስዊዝ ካናል ካምፓኒ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። የ99 አመታት ኮንትራትም በውሃ መስመሩ እና በዙሪያ አካባቢው ላይ ተሰጥቶት ነበር። ድርጂቱ የ13 ባለሙያዎች ስብስብ የሆነ ኮሚሽን አቋቋመ። ከባለሙያዎቹ አንዱ አሎይስ ኔግሬሊ መሪ ሲቪል ኢንጂነር ነበር።
ኔግሬሊ የስዊዝ ካናልን ንድፍ በመስራት በኩል የምሪነት ሚና ነበረው። የባለሙያዎች ስብስቡ ሪፖርቱን በ1940ዎቹ መጨረሻ አጠናቀቀ። ግንባታው በሰሜነኛው ክፍል በሰኢድ ወደብ በኩል ተጀመረ።
የቁፋሮ ስራው ግን አስር ዓመታትን የፈጀ ነበር። 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችም ተሳትፈውበታል። የሚያሳዝነው ግን በስራው ላይ ሲሳተፉ የነበሩት የእንግሊዝ፣ የአሜሪካ እና የፈረንሳይ ድርጂቶች ባሪያ አሳዳሪዎች ነበሩ።
በዚህ ትልቅ ስራ ላይ በ10 ሺዎች የሚቆጠር ሰዎች በኮሌራ እና ሌሎች ምክኛቶች ህይወታቸው አልፏል። የፖለቲካ ትኩሳቶችም የስዊዝ ቦይን ስራ አስተጓጉለውታል።
ግብጽ በእንግሊዝም በፈረንሳይም ትተዳደር የነበረ መሆኑ ደግሞ በቅኝ ገዥዎቹ ላይ ተደጋጋሚ አመጾች ይነሱ ነበር። በወቅቱ ከነበረው የግንባታ ቴክኖሎጂ ውስንነት ጋር ተዳምሮ የስዊዝ ቦይ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ ወደ 100 ሚሊዮን ብር እንዲደርስ አድርጓል።
ይህም ከመጀመሪያው ግምት በእጥፍ ይበልጣል። የባህር ሰርጡን ለመናድ ከፍተኛ ጉልበት ይጠይቅ ስለነበር በፈረስ የሚሳቡ ተሽከርካሪዎችን ኋላም ባቡሮችን በዋናነት እንግሊዝ ተጠቅማለች። እንግሊዝ ከቅኝ ግዛቶቿ የኤስያ ሀገራት ህንድ እና ፓኪስታን ጋር ከፍተኛ ንግድ ታካሂድ ነበር።
የግብጽ እና ሱዳን ከዲቭ ወይም መሪ የነበረው ኢስማኤል ፓሻ የስዊዝ ካናልን በ1862 ዓ.ም. በይፋ ከፈተ። የአውሮፓ እና የኤስያ የባህር ላይ የንግድ ልውውጥን የሚያሳጥረው አዲሱ መተላለፊያ መስመር የስዊዝ ቦይም ለመርከብ ጉዞ ክፍት ሆነ።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታትም በስዊዝ ቦይ ላይ የተደረጉት የባህር ላይ ምልልሶች ከተጠበቀው በታች ቢሆኑም የዚሁ አዲስ መስመር መከፈት በዓለም ንግድ ላይ የራሱን ተጽዕኖ አሳድሯል።
አውሮፓውያኑ አፍሪቃን በቅኝ ግዛት እንዲቀራመቱም የራሱን ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። በይፋ ከተከፈተ በኋላ ለ87 ዓመታት በዋናነት በእንግሊዝ እና ፈረንሳይ ቁጥጥር ውስጥ ቆይቷል።
ከመካከለኛው ምስራቅ ነዳጅ ለመውሰድም ርካሽ መንገድ ሆኖ አገልግሏል። ግብጽ ለስዊዝ ቦይ የባለቤትነት ቅርበት ቢኖራትም በቅኝ ግዛት ስር ነበረች። ኋላም የግብጹ መሪ ጋማል አብደል ናስር ለትልቁ የአስዋን ግድብ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ እንዲውል በሚል በዛሬዋ ዕለት በ1948 ዓ.ም. የግብጽ ነው ሲሉ ከእንግሊዝ እና ፈረንሳይ ነጥቀዋል።
ይሄው ድርጊታቸውም የስዊዝ ቦይን በግብጽ እጅ የማስገባት መንገድን ጠርጓል። እንግሊዝ፣ፈረንሳይ እና እስራኤል ግብጽን አጥቅተው የስዊዝ ቦይን ቢነጥቁም የሶቭየት ህብረት፣ የአሜሪካ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጂት ግፊት ሀገራቱ የስዊዝ ቦይን ለቀው ለግብጽ እንዲያስረክቡ አስገድዷቸዋል።
በዓለም የንግድ ሁኔታ ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳደረው ብሎም የ193 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው የስዊዝ ቦይ በየቀኑ በአማካይ 50 ያክል መርከቦችን የሚያስተናግድ ሲሆን በዓመት ከ300 ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት ይጓጓዝበታል።
በአብርሃም በለጠ
2022-07-25
