ሀገሬ ቲቪ

የእንክብካቤ ክፍተት የሚታይበት የችግኝ ተከላ ዘመቻ

ኢትዮጵያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በዘመቻ መትከል ከጀመረች ዘንድሮ አራት ዓመታትን አስቆጥራለች። የዘንድሮን ሳይጨምር ባለፉት ሦስት ዓመታት 17 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኞችን በሀገር አቀፍ ደረጃ መተከላቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

እነዚህ ችግኞች መተከላቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለማረቅ የራሱን ሚና መጫወቱ እንዳለ ኾኖ ችግኞቹ በምንዓይነት ጥንቃቄ መተከል አለባቸው፣ ምን ዓይነት ቅድመ ኹኔታዎች ሊሠሩ ይገባቸዋል፣ ችግኞቹ ከተተከሉ በኋላስ የሚደረገው እንክብካቤ ምን ይመስላል የሚሉ ጉዳዮች በሰፊው ሲነሱ አይስተዋልም።

እኛም ይህን ጥያቄ አንግበን አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራምን ከሚያስተባብሩ ተቋማት አንዱ ወደኾነው ወደ ኢትዮጵያ ደን ልማት ጎራ ብለናል።

ተቋሙ በቅድመ ችግኝ ተከላም ኾነ በድህረ ተከላ ለባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጥ በተቋሙ የደን ልማት ዳይሬክቶሬት ጄነራል አቶ ቢታው ሽባባው ተናግረዋል ይሁን እንጂ በተነሣው ጉዳይ ላይ ክፍተቶች የሉም ማለት አይደለም ብለዋናል።

በተጨማሪ የኢትዮጵያ ደን ልማት ችግኞቹ ወደ ተተከሉበትክልሎች እና አካባቢዎች በመሔድ ችግኞቹ ከምን ደረሱ የሚለውን ክትትል እንደሚያደርግ አቶ ቢታው ነግረውናል። ቢኾንም የተወሰኑ ቦታዎች የተተከሉ ችግኞች ከመጥፋት ጀምሮ የሚያዩ ችግሮ ስለመኖራቸው ገልጸውልናል።

ችግኞች ከተተከሉ በኋላ ዞር ብሎ የማየቱ እና የመንከባከቡ ነገር ነገር እንዴት ይታያል ስንል ተመሳሳይ ጥያቄ በጉለሌ የዕጸዋት ማዕከል የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር የኾኑትን አቶ መክብብ ማሞን ጠይቋል።

አንድ ችግኝ አፍልቶ ለተከላ ለማድረስ ብዙ ወጪ እንዳለበት የተናገሩት አቶ መክብብ ከዚህ ረገድ ችግኞቹን ከተከሉ በኋላ እንክብካቤ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸውልናል።

ሌላው ችግኞችን ከተተከሉ በኋላ መደረግ ስለሚገባቸው የእንክብካቤ ሥራዎች በተጨማሪ በስፋት ሲነገር የማይስተዋለው ጉዳይ ቢኖር ከተከላ በፊት መሠራት ስለሚገባቸው ቅድመኹኔታዎች ናቸው።

እንደ አቶ መክብብ ገለጻ አንድ ችግኝ ከመተከሉ በፊት መደረግ የሚገባቸው ነገር በስፋት የማይስተዋሉ በርካታ ቅድመ ሥራዎች አሉ ብለውናል።

አኹን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሔደ ያለው የችግኝ ትከላ ዘመቻ መጨመሩ የሥራ እድል እንዲፈጠር በር መክፈቱን አቶ መክብብ ነግረውናል።

እንደአብነትም ከዚህ ቀደም የጉለሌ የዕጽዋት ማዕከል ዓመታዊ የችግኝ ብዜት ከፍተኛው 90 ሺህ ነበር። አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ ግን የችግኝ ብዜቱ ወደ 7 መቶ ሺህ ከፍ ብሏል። ይኽም በርካታ ወጣቶች በችግኝ ማፍላቱም ኾነ በሌላው የሥራ መስክ እንዲሳተፉ አድርጓቸዋል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-07-26