በኢትዮጵያ የትንባሆ ጭስ ተጋላጭ በመሆን ጤናቸው የሚቃወስ ዜጎች ቁጠር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በ2011 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትንባሆን የተመለከተ ጠንካራ ነው የተባለለት ሕግ ማውጣቱ ይታወሳል።
በዚህ ሕግ መዝናኛ ቦታዎች፣ መጓጓዣ መያዣ ሥፍራዎች፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው የአደባባይ ቦታዎች ላይ ትንባሆ ማጨስን ይከለክላል። ነገር ግን እነዚህ ሕጎች በሚገባ ተፈጻሚ ኾነዋል ለማለት እንደማያስደፍር ብዙዎች ይናገራሉ።
እኛም በጉዳዩ ላይ ትዝብታችሁን አጫውቱን ስንል የተወሰኑ የከተማዋን ነዋሪዎች ጠይቀን ነበር። ሕጉ በሚፈለገው መጠን ተፈጻሚ ኾኗል ማለት እንደማይቻል ነው የነገሩን።
በሀገራችን ትንባሆን ከማጨስ ጋር ተያይዞ በሚመጡ በሽታዎች በዓመት 17 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ። በዋናነት ይህን የማኀበራዊ ጤና ቀውስ ለማስወገድ ነው የትንባሆ ቁጥጥር ሕጉ መውጣቱ።
ጉዳዩ በዋናንተ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ምግብ መድኃኒት ባለሥልጣንን ሕጉ ላይ ስለተነሳው የአፈጻጸም ክፍተት ጠይቀናል በተቋሙ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ደኀንነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የኾኑትን ወ/ሮ አስናቀች ዓለሙ ሕጉ በተወሰነ መልኩ ጥሩ አፈጻጸም ቢኖረውም የሚቀሩ ሥራዎች አሉ ብለውናል።
የኢትዮጵያ ምግብ መድኃኒት ባለሥልጣን በዋናነት የጉዳዩ ባለቤት ቢሆንም የወጣው ሕግ በሚፈለገው ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ እንዲሆን ሁሉም አካል ሊያግዘኝ ይገባል ብሏል። ይህ የትንባሆ ቀጥጥር ሕግ፤ በሕግ ባለሙያዎችስ እንዴት ይታያል አቶ ቢኒያም እንድሪስ የሕግ ባለሙያ ናቸው በተነሳው የትንባሆ ቀጥጥር ሕግ ላይ አፈጻጸሙን ከተመለክትን ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ እናገኘዋለን ብለውናል።
የትንባሆ ቁጥጥር ሕግ ትንባሆ እንዳይጨስባቸው በተወሰነባቸው ቦታዎች ተፈጻሚ እንዲሆን ኃላፊነቱን ለቦታው ባለቤት ብቻ መስጠቱ አፈጻጸሙ ላይ ክፍተት ሊፈጥር እንደቻለ አቶ ቢኒያም ተነግረዋል።
አንድ ሕግ በሚገባ ተፈጻሚ እንዲሆን እና ማኀበረሰቡም በሚገባ እንዲረዳው ግንዛቤ የማስረጽ ሥራ መሰራት ያለባቸው ቅድመሁኔታዎች እንዳሉ የህግ ባለሙያዉ ገልጸውልናል።
በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ትንባሆ አጫሾች እንዳሉ ጥናቶች ያመላክታሉ።
በሙሉጌታ በላይ
2022-07-27
