ሀገሬ ቲቪ

ዕለቱን ከታሪክ- የመጀመሪያው የንግድ ጄት አውሮፕላን

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፕላን መገኘት የሰዎች የጉዞ ታሪክ ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል። የጀት ሞተር ለአውሮፕላኖች መዋል ደግሞ የአውሮፕላኖች የጉዞ ፍጥነትን በእጥፍ አሳድጓል።

73 ዓመታትን መለስ ስንል የመጀመሪያው የንግድ ጄት አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ማድረጉን እናገኛለን። ይሄው ጄት አውሮፕላን ኮሜት የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ነው።

የጀት ሞተር መፈጠር በአውሮፕላን ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። የአውሮፕላን ጉዞ ፍጥነትን በእጥፍ ከመጨመሩም በላይ የአውሮፕላኖች የጉዞ ከፍታም እንዲጨምር አድርጓል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመጀመሪያው የጀት አውሮፕላን ዴ ሃቪላንድ ኮሜት የሙከራ በረራውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገው በዛሬዋ ዕለት በ1941 ዓ.ም. ሆኖ እናገኛለን።

ይሄው ኮሜት የተሰኘችው ጄት የእንግሊዛዊው የአውሮፕላን ዲዛይነር እና የበረራው ኢንዱስትሪ ፋና ወጊ የሆነው የሲር ጆፍሬይ ዲ ሀቪላንድ ፈጠራ ነበረ።

ዲ ሃቪላንድ ቀደም ብሎ የሞተር ብስክሌቶችን እና ባሶችን ዲዛይን የሚያደርግ ሰው ነበር። በ1900 ዓ.ም. ዊልበር ራይት በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፕላንን ለህዝብ ካስተዋወቀ በኋላ የራሱን አውሮፕላን የመገንባት ሀሳብ አድሮበታል።

የመጀመሪያዎቹ የአውሮፕላን ፈጣሪዎች የራይት ወንድማማቾች እውቅ የመጀመሪያ በረራቸውን በኪቲ ሃውክ በሰሜን ካሮሊና አሜሪካ በ1896 ዓ.ም. ነበር ያደረጉት።

በዊልበር ራይት የአውሮፕላን ስራን ለአውሮፓ ማስተዋወቅ የተነሳሳው ዴ ሃቪላንድ የመጀመሪያ አውሮፕላኑን በተሳካ ሁኔታ ዲዛይን ማድረግ ብሎም ማብረር ችሏል። በ1912 ዓ.ም. የራሱን ማምረቻ ድርጅት ከመክፈቱ አስቀድሞም ለእንግሊዝ አውሮፕላን አምራቾች ይሰራ ነበር።

የሃቪላንድ የአውሮፕላን ማምረቻ ድርጅት በበረራ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀለል ያሉ እና ፈጣን ሞተሮችን በማበልጸግ በኩል የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የተሻሻሉ አውሮፕላኖችን በማምረትም ዕውቅ ለመሆን በቅቷል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመን ተዋጊ ጄቶችን በመጠቀም ተቀዳሚ ሆናለች። በጦርነቱ አመታት ዲ ሃቪላንድ ተዋጊ አውሮፕላኖችን በመንደፍ አገልግሏል። ለዚህ አበርክቶውም በውትድርና እስከመሾም ደርሷል።

ከጦርነቱ በኋላ ዲ ሃቪላንድ ትክረቱን የንግድ ጄቶች ላይ አድርጓል። ኮሜትን እና የጀት ሞተርን ማበልጸግ ላይ ትኩረቱን አድርጓል። ከ73 ዓመታት በፊትም በ1941 ዓ.ም. የጄት አውሮፕላኑን ኮሜትን ለሙከራ አበረረ። የተሳካ ሙከራም ማድረግ ቻለ። በዚህም ፈጠራው የበረራ ኢንዱስትሪውን ቀይሯል። ፈጣን አውሮፕላኖችን የማምረት መንገድን ጥርጓል።

ኮሜት የመጀመሪያ ሙከራዋን ካደረገች በኋላ ለሶስት ዓመታት በሙከራ እና በልምምድ በረራ ቆይታለች። ኋላም ከአራት አመታት በኋላ የእንግሊዝ የአውሮፕላን ተቆጣጣሪ ድርጅት በዓለም የመጀመሪያዋ የንግድ ጄት የሆነችውን ኮሜት 1Aን በ44 መቀመጫዎች ከለንደን ወደ ጆሃንስበርግ እንድትበር በማድረግ የመጀምሪያውን የንግድ ጄት አገልግሎት አስተዋውቋል።

ኮሜት 772.5 ኪ.ሜ. በሰዓት መጓዝ የምትችል ነበረች።

በአብርሃም በለጠ
2022-07-27