ምዕራባዊያን ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ በአፍሪካ አህጉር ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ከፍተኛ ፉክክር ላይ ናቸው ይላሉ ከአጃንስ ፍራን ፕረስ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ምሁራኖች።
ከስሞኑን እንደጉድ ወደ አፍሪካ እየጎረፉ ነው ለአብነትም የሩሲያ፣ የፈረንሳይና የአሜሪካ መሪዎች በዩክሬን ጦርነት ላይ ያላቸውን አቋም እንድትደግፍ አፍሪካን እያቋረጡ ነው።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እና የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚህ ሳምንት በርካታ የአፍሪካ ሀገሮችን እየጎበኙ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ባለፈው ሳምንት ወደ ኬንያና ሶማሊያ ሄደዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ጋና እና ዩጋንዳ ይሄዳሉ።
መልካም አስተዳደርን የሚያበረታታ የዴሞክራሲ ሥራዎች ዳይሬክተር የሆኑት ዊልያም ጉሜዴ “አዲስ ቀዝቃዛ ጦርነት በአፍሪካ ውስጥ እየተካሔደ ያለ ይመስላል ይላሉ። ተቀናቃኝ ወገኖች ተፅዕኖ ለማግኘት እየጣሩ ነው” ብለዋል።
ላቭሮቭ በድርቅና በረሃብ በተጠቃችው አህጉር ላይ በተጓዙበት ወቅት ምዕራባውያንን እንደ ክፉ አድርገው ለመግለጽ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የምዕራቡ ዓለም መሪዎች ደግሞ ምግብን እንደ መሣሪያ በመጠቀምና የድል ጦርነት በማካሄድ ላይ ናቸው በማለት ሲወነጅሉ ቆይተዋል። እነዚህ ቃላት ከቅኝ ግዛት በኋላ በነበሩት የአፍሪካ ሀገሮች የሚገኙ አድማጮችን ለመማረክ የሚሰሉት ቃላት ናቸው።
በፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን አገዛዝ ሩሲያ በአፍሪካ ድጋፍ ለማግኘት ለበርካታ ዓመታት ስትሠራ ቆይታለች። የሶቭየት ሕብረት የቅኝ ግዛት አገዛዝን ለማስቆም የሚታገሉ በርካታ የአፍሪካ እንቅስቃሴዎችን በደገፈችበት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የነበረውን ወዳጅነት በማጠናከር ላይ ትገኛለች።
“አሁን ያ ዘመቻ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል” ይላሉ ጉሜዴ።
ሞስኮ በአፍሪካ ላይ ያሳደረችው ተፅዕኖ የታየው በመጋቢት ወር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያን ዩክሬይን ወረራ ለማውገዝ ድምፅ በሰጠበት ወቅት ነበር።
28 የአፍሪካ ሀገራት የአቋም መግለጫውን ቢቀበሉም በአህጉሩ ውስጥ የሚገኙ 25 ሀገሮች ግን ድምፀ ታዕቅቦ አድርገዋል፤ አሊያም ጨርሶ ድምፅ አልሰጡም ።
የሩሲያ ከፍተኛ ዲፕሎማት በዚህ ሳምንት ግብጽን፣ ኮንጎን፣ ኡጋንዳን እና ኢትዮጵያን ጎብኝተው፣ ወዳጅነት ለመመሥረት ቃል በመግባት እና የዩናይትድ ስቴትስን እና የአውሮፓ ሀገሮችን "ግድ የለሽ" የአካባቢ ፖሊሲዎችን በመከተል የምግብ ዋጋ ከፍ በማድረግ ላይ ናቸው በማለት ከሰዋል።
ላቭሮቭ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ “በዩክሬን ያለው ሁኔታ በምግብ ገበያዎች ላይ ተጨማሪ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል፤ ነገር ግን በሩሲያ ልዩ እንቅስቃሴ ምክንያት አይደለም። በምዕራቡ ዓለም ሙሉ በሙሉ በቂ ምላሽ ባለመሰጠቱ ነው” ሲሉ ይከላከላሉ።
የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዮኤሪ ሙሴቬኒ ለበርካታ ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስ አጋር ቢሆኑም በወረራው ምክንያት ሩሲያን ለመተቸት ፈቃደኛ አልሆኑም እንዲያውም ላቭሮቭን ሞቅ ባለ ስሜት ተቀብለዋል ።
በተጨማሪም ሩሲያ ቀደም ሲል ሩሲያ ቱዴይ ብላ ትጠራው በነበረው አር ቲ በሚባለው የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያዋ አማካኝነት የአፍሪካን የሕዝብ አስተያየት እየተቀበለች ነው። አር ቲ በጆሃንስበርግ አዲስ ቢሮ እንደሚከፍት አስታውቋል።
የፈረንሳዩ ማክሮን በአፍሪካ ጉብኝታቸው ላይ ክሬምሊን ጦርነቱን ለመደገፍ እንደ አር ቲ ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በመጠቀም ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ወንጀል ፈጽማለች ብለዋል።
በተጨማሪም ከዩክሬን እህል ወደ ውጭ እንዳይላክ በማደናቀፍ ክሬምሊን ዓለምን አስነውሮታል የሚል ክስ አሰምተዋል።
ማክሮን አፍሪካውያን ከሩሲያ ጎን እንዳይሰለፉ አቤቱታ አቅርበዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ ሳማንታ ፓወርም ልክ እንደ ማክሮን ሁሉ ሩሲያን ሳትወርፍ ዝም አላለችም።
“የዩክሬንን የእህል ምርት በመዝጋት እናም የሩሲያን የማዳበሪያ ንግድ የመገደብ የፑቲን እርምጃ በኬንያ ህዝብ ላይ እና በመላው ዓለም በሚገኙ ሀገራት ላይ ስቃይ አስከትሏል” ብለዋል።
“ፑቲን የራሱን ሁኔታ ለመጥቀም ሲል የኬንያን ሕዝብ እየጎዳ ነዉ።” ሲሉ ተደምጠዋል።
ታዲያ ይህ ሁሉ ሽኩቻ አፍሪካን ለመጥቀም ይሆን?
በፍሬሕይወት ታደሰ
2022-07-28
