ሀገሬ ቲቪ

የናሳ መቋቋም

በጠፈር ምርምሩ ዘርፍ ናሳ ግዙፍ ተቋም ነው። ትልልቅ አበርክቶዎችንም አምጥቷል። ይሄው ተቋም እንዲቋቋም የተደረገው በ1950 ዓ.ም. በዛሬዋ ዕለት ነበር። የአሜሪካ ኮንግረስ ተቋሙ እንዲመሰረት ያደረገው ለሶቭየት ህብረት የስፑትኒክ 1 የተሳካ ተልዕኮ ምላሽነት ነበር።

ሶቭየት ህብረት በ1949 ዓ.ም. በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነችውን ሳታላይት ስፑትኒክ 1ን ወደ ጠፈር መላክ ችላለች። 83 ኪ.ግ ትመዝን የነበረችው ስፑትኒክ ወደ ጠፈር ተልካ በመሬት ምህዋር ዙሪያ መሽከርከር መቻሏ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካን አስደንግጧል።

አሜሪካውያኑ ሶቭየት ህብረት ከአውሮፓ የኒውክሌር ሚሳኤሎችን ወደ አሜሪካ መላክ ቢያስችላትስ ብለው ስጋት አድሮባቸዋል። ለዚህም አሜሪካ ከሶቭየት ጋር የነበራትን የቴክኖሎጂ ፉክክር ለማሳደግ እና ምላሽ ለመስጠት ተነሳች። የዩኤስ-ሶቭየት የጠፈር ፉክክርም አንድ ብሎ ጀመረ።

ሶቭየት ስፑትኒክ ሁለትን ውሻ ይዛ እንድትመጥቅ በማድረግ ሳታላይት ማስወንጨፏን ደገመች። አሜሪካ ቬንግያርድ የተሰኘችውን የራሷን ሳታላይት ብታስወነጭፍም ሳታላይቷ ብዙም ሳትቆይ ፈነዳች።

በ1950 ዓ.ም. ግን ነገሮች መሻሻል ጀመሩ። ኤክስፕሎረር 1 የተሰኘችው የአሜሪካ ሳታላይት በመሬት ዙሪያ መሽከርከር ቻለች።

አሜሪካ የጠፈር ምርምሩ ፉክክሩን የሚመራ ተቋም መመስረት ፈልጋለች። የአሜሪካ ምክር ቤት የሀገሪቱን የጠፈር ምርምር የሚያስተባብር ብሄራዊ የበረራ እና የጠፈር አስተዳደርን ናሳ እንዲቋቋም በዛሬዋ ዕለት ከ64 ዓመታት በፊት አጸደቀ።

በሐምሌ ወር 1950 ዓ.ም. አሜሪካ ናሳ እንዲቋቋም በመወሰን በጠፈር ምርምር ዘርፉ ፉክክሯን ለማሳደግ መፈለጓን አሳየች። የሲቪል ድርጅት የሆነው ናሳ የአሜሪካን የጠፍረ እንቅስቃሴዎች እንዲያስተባብር ስልጣን ተሰጠው።

ናሳም የጠፈር ምርምር ስራውን ጀመረ። የተለያዩ ሰብዓዊ እና መካኒካዊ ጉዞዎችን ወደ ጠፈር እንዲደረጉ በማድረግ ስለ ስርዓተ ጸሃይ ስለ ህዋ ለሰው ልጆች መረጃዎችን በማድረስ ሲያገለግል ቆይቷል። የላካቸው ሳታላይቶችም ዓለምን ከአየር ትንበያ እስከ አለም አቀፍ የተግባቦት ምንጭነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

ለስፑትኒክ 1 የሶቭየት ስኬት ምላሽነት የተቋቋመው ናሳ በበረራ ቴክኖሎጂዎች እና የህዋ ምርምር ዘርፍ ላይ ስልጣን ተሰጥቶታል። በፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ አስተዳደር የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ትልቅ መሻሻል አስመዝግቧል።

ይህም የሆነው የኬኔዲ አስተዳደር ወደ ጨረቃ የመጓዝ እቅድን በማስተዋወቃቸው ነበር። ይሄው እቅድ በ1950ዎቹ ትልቅ መሻሻል እንዲያሳይም ምክንያት ሆኖታል።

በ1961 ዓ.ም. በአፖሎ 11 ተልዕኮ ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃን እንዲረግጥ በማድረጉ ናሳ አሜሪካን ወደ ጨረቃ በመጓዝ ቀዳሚ አድርጓታል።

ቀጥለውም እንደ ቫይኪንግ፣ ማሪነር፣ ቮየጀር እና ጋሊልዮ የመሳሰሉ ሰው አልባ ተልዕኮዎቹ ሌሎች የስርዓተ ጸሃይ አካላትን ለመለየት አስችለዋል።

ከመጀመሪያው ወደ ጨረቃ የመጓዝ ተልዕኮ ጀመሮ ናሳ በጠፈር ምርምሩ ዘርፍ የአለም አቀፉን የጠፈር ተቋምን መገንባትን ጨምሮ ትልልቅ አበርክቶዎችን አምጥቷል።

የመሬት የተፈጥሮ ሀብቶችን መመዝገብ የሚያስችሉ እንደ ላንድሳት ያሉ ሳታላይቶችን ወደ ጠፈር በመላክም ናሳ ለዓለም አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በተጨማሪም በተለመደው የጠፈር መንኮራኩር ሊከናወኑ የማይችሉ ተልእኮዎችን ማከናወን የሚችል እንደገና መጠቀም የሚችል የጠፈር መንኮራኩር ማዘጋጀት ችሏል።

የ64 ዓመቱ ናሳ ከሶቭየት ጋር ለነበረው የጠፈር ምርምር ፉክክር ምላሽነት ተቋቁሞ ዛሬ ላይ በጠፈር ምርምሩ ዘርፍ ቀዳሚ እንደሆነ ያለ ድርጅት ነው።

በአብርሃም በለጠ
2022-07-29