አሳዳጊዎቹ ዴክስተር እያሉ ይጠሩታል በአሜሪካ ኮሎራዶ የሚኖር የ 7 ዓመት ዉሻ ነዉ፡፡ ዴክስተር በቅልጥፍናውና ለሰው ልጅ ባለው ፍቅር በቤተሰቡ ውስጥ ተወዳጅ እንደሆነ አሳዳጊው ትናገራለች ።
ታድያ በአንድ ወቅት የቤተሰቡ አባላትን ሀዘን ውስጥ የከተተ ነገር ይፈጠራል። ዴክስተር ከቤት አምልጦ የተሽከርካሪ መንገድ ላይ በመግባት አደጋ ይደርስበታል ።
በአደጋውም ሁለት የፊት ለፊት እግሮቹ ክፉኛ ተጎዱ። ዴክስተር ከደረሰበት ጉዳት በኋላ እንደ መሰሎቹ በ አራት እግሩ መራመድ ተሳነው።
ይህን የተመለከቱት አሳዳጊዎቹም ለውሻው መንቀሳቀሻ ይሆነው ዘንድ ዊልቸር ገዝተው ያቀርቡለታል ። ነገር ግን ይህ ውሻ ባለመድኩት ነገር አልንቀሳቀስም መሰል የተገዛለትን ዊልቸር እግር ማድረግ አልፈልገም ።
ታዲያ አንድ ቀን ብቻውን ከተቀመጠበት ቀና በማለት በተረፉለት ሁለት የኋላ እግሮቹ ለመራመድ ሲሞክር በድንገት አሳዳጊው ትመለከተዋለች።
ይህን ፍላጎቱንም ለማሳካት ባደረገችለት ዕገዛም ዴክስተር ባሉት ሁለት እግሮች ቀስ በቀስ መራመድ ጀምረ ።
ይህ ተወዳጅ ውሻ እንደሰው በሁለት እግሮቹ ለመራመድ ጊዜ አልፈጀበትም ። አሁን ላይ ልክ እንደቀድሞው ህይወቱ ያለማንም አጋዥ ከአሳዳጊው ጋር አንገቱን ወዲያ እና ወዲህ እያዞረ በጎዳናዎች ላይ እንደ ልቡ መንሸራሸር ጀምሯል ።
የዚህን ውሻ ታሪክ ይዞት የወጣው ኦዲቲ ሴንትራልም ዴክስተር ዐለም ላይ ለሚኖር የሰው ልጅ ሁሉ የጥንካሬ ምሳሌ ነው በተለይ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከዚህ ውሻ ወድቆ መነሳትን ሊማሩ ይገባል ይላል ።
ይህ የዴክስተር ታሪክ በብዛት ያልተለመደ ቢሆንም ከጥቂት አመታት በፊት ፌዝ የምትባል ሁለቱንም የፊት እግሮቿን ያጣች ዉሻ ልክ እንደ ዴክስተር በኋላ እግሮቿ መንቀሳቀስ በመጀምሯ ለብዙዎች አርአያ እና ምሳሌ ሆና በስሟ ፋዉንዴሽን ተክፍቶ እንደነብረ ኦዲቲ ሴንትራል በጽሁፉ ማጠቃሊያ አስፍሯል ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-07-29
