ሀገሬ ቲቪ

ከዩክሬን ለመጀመሪያ ጊዜ እህል የጫነች መርከብ ተንቀሳቀሰች

ከ 150 ቀናትን በላይ በዘለቀው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በርካታ ጉዳዮች ሲነሱ እና ሲጣሉ ከርመዋል።

ሀገራቱ የገቡበት ጦርነት የኹለቱ መኾኑ ቀርቶ የዓለም ጉዳይ ከኾነም ቆይቷል። በተለይም ሁለቱም ሀገራት የበርካታ ሀገራት የቀለብ ምንጭ መኾናቸውን እንደአብነት ማንሳት ይቻላል። በዛሬው ዕለት ታዲያ ከዩክሬን ኦዴሳ ወደብ እህል የጫነች መርከብ ወደ ሊባኖን ጉዞ ጀምራለች።

ራዞኒ የተሰኘችው እና የሴራሊዮንን ባንዲራ ስታውለበልብ ነበር የተባለችው መርከብ ሰፋ ያለ የበቆሎ ምርትን ጭና ከወደቡ እንደተነሳች ተሰምቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርከቧ የጫነችው የበቆሎ መጠን ከ 26 ሺህ ቶን በላይ እንደሚሆን አስታውቋል።

ለዚህ እንቅስቃሴ መሳካት የሩሲያ አውንታዊ ፈቃድ የታከለበት እንደኾነ ይገለጻል። ሩሲያ ከካቲት ወር ጀምሮ የዩክሬንን ወደቦች ተቆጣጥራ ትገኛለች፣ ነገር ግን ሁለቱ ወገኖች የሚደረጉ ማንኛውንም ጭነቶች ለመቀጠል ስምምነት አድርገዋል።

ስምምነቱ ዓለም አቀፉን የምግብ ቀውስ የሚያቃልልና የእህልን ዋጋ እንዲቀንስ የሚያስችል ቸር ወሬ ነው ሲሉ በርካታ አካላት እየደገፉት ይገኛሉ።

በስንዴ እና በሌሎች ምርቶቿ የምትታወቀው ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷ ወደ ሌሎች ሀገራት ትልካቸው የነበሩ ምርቶች እንድታቋርጥ ተገዳለች በዚህ እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ቀውስ ሊከሰት ችሏል። በርካት ምግብ ነክ ምርቶች ዋጋቸው የሚቀመስ ሊኾን አልቻለም።

ሁለቱ ሀገራት ከገቡበት ጦርነት እንዲወጡና የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ በተደጋጋሚ በዓለም መንግሥታት ጥሪ ሲደረግላቸው ነበር። ሌላው በኢህ ጉዳይ ልዩ ስምምነት አድርገው ወደቦች ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ነበር።

ሁለቱ ሀገራት ጦርነተ ከጀመሩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ጠዋት እህል የጫነችው መርከብ ከዩክሬን ወደብ ተንቀሳቅሳለች።

በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙ ሦስት ወደቦች ማለትም ኦዴሳ ፣ ኮርኖሞርስክ እና ፒቭደንኒ ወደ ውጭ የሚላኩት ወደቦች ዋነኛ ማዕከል እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ዛሬ የተንቀሳቀሰችው መርከብ የተነሳችበት የኦዴሳ ወደብ ከቀናት በፊት ሩሲያ ጥቃት አድርሳበት ነበር። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪም ጥቃቱን አረመኔያዊ’ ሲሉ ማውገዛቸው ይታወሳል።

የዩክሬንን የእህል ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ከተደረገ ከሰዓታት በኋላ ጥቃቱ መድረሱ የተደረሰው ስምምነት ላይሳካ ይችላል የሚል ሥጋትን አንዣቦ ሰንብቷል።

በዛሬው ዕለት ግን ይህ ስጋት እውን እንደማይኾን በቆሎ የጫነችው መርከብ መንቀሳቀሷ ማረጋገጫ ኾኗል። ይህ ብቻ አይደለም በመጪዎቹ ሳምንታት ሌሎች 16 መርከቦች ከኦዴሳ ወደብ እንደሚነሱ ተጠቁሟል።

ራዞኒ የተሰኘችው መርከብ ነገ ቱርክ ኢስታንቡል ከደረሰች በኋላ አስፈላጊው ምርመራ እና ፍተሻ ተደርጎ ወደ መዳረሻዋ ሊባኖን ትቀጥላለች። ይህ የሚኾነው በዚህ አጋጣሚ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል እንደኾነ ተነግሯል።

ዩክሬን ከአጋር ሀገሮቿ ጋር በመኾን የዓለም ርሀብን ለመከላከል እርምጃ ወስዳለች ሲሉ የዩክሬን መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ተናግረዋል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-08-01