ሀገሬ ቲቪ

አባባ ተስፋዬ

አባባ ተስፋዬ ለ42 ዓመታት በኢትዮጵያ ቴ.ቪ. የልጆች ፕሮግራምን በአባትነት ስሜት ሲያቀርቡ በሚሊዮኖች የያኔው ልጆች ልብ ውስጥ ትዝታቸውን ያሳረፉ አባት ናቸው።

በተዋናይነት በአዲስ አበባ ባህል እና አዳራሽ ብሎም ብሄራዊ ቴያትር ከሶስት አስርት አመታት በላይ አገልግለዋል። አባባ ተስፋዬ ያረፉት በ93 ዓመታቸው ሰኞ ሐምሌ 24፣ 2009 ነበር። እኛም በእለቱን ከታሪክ ልናወሳቸው ወደድን።

አባባ ተስፋዬ በሙሉ ስማቸው አቶ ተስፋዬ ሳህሉ ተብለው ይታወቃሉ። ከአባታቸው ኤጀርሳ በዳኔ እና ከእናታቸው ዮንዢ ወርቅ በለጤ ሰኔ 20፣ 1916 ዓ.ም በቀድሞ ባሌ ክፍለ ሃገር ከዶ የተሰኘ አካባቢ ነበር የተወለዱት።

የአባባ ተስፋዬ የትምህርት ህይወት የጀመረው በአምስት አመታቸው ነበር። አባታቸው ወደ ጎባ ሲጓዙ አብረው በመጓዝ በዚያው የአብነት ትምህርት ጀምረዋል።

በጎባ የመጀመሪያ ትምህርታቸውን የጀመሩት አባባ ተስፋዬ ወላጆቻቸው በስራ ምክንያት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ይዘዋወሩ ስለነበር በጊኒር ኋላም በሐረር የፈረንሳዮች ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

በ14 ዓመታቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸው ትምህርታቸውን በኮከበጽባህ ትምህርት ቤት ቀጥለዋል።

ፋሽስት ጣሊያን ሀገራችን ወርሮ በርካታ ሰዎችን ሲፈጅ ከሟቾች መካከል የአባባ ተስፋዬ ወላጆችም ነበሩበት። ምንም እንኳን ገና በልጅነታቸው እናትና አባታቸውን በሞት ቢያጡም አባባ ተስፋዬ አንቱ የሚያስብላቸውን ስራ ወደ ኋላ አላሉም።

በወላጆቻቸው ሞት ለከፍተኛ የህይወት ፈተና የተጋለጡት አባባ ተስፋዬ በልጅነታቸው ከአካባቢያቸው ከቤተሰቦቻቸው ባገኙት የስለላ፣ ቀረርቶ እና መሰል ትውፊታዊ ክዋኔዎችን ከነበራቸው የኪነጥበብ ፍላጎት አስተባብረው የኪነ ጥበብ ዘርፉን ተቀላቀሉ።

የአዲስ አበባ መስተዳድር ባህል እና ቴያትር አዳራሽ ማስተዋቂያ ካወጣ በኋላ አባባ ተስፋዬ የኪነ ጥበብ ቤቱን በተዋናይነት ተቀላቀሉ። ያኔ የ11 ብር የወር ተከፋይ ነበሩ። ኋላም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴያትር አገልግለዋል።

አባባ ተስፋዬ በትወናው ከ70 በላይ ቴያትሮችን ተጫውተዋል። ከተሳተፉባቸው ቴያትሮችም ሀሁ በስድስት ወር፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ ኤዲፐስ ንጉስ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ ኦቴሎ፣ ዳዊ፣ አስቀያሚዋ ልጃገረድ ይገኙበታል።

በአዲስ አበባ ባህል እና ቴያትር አዳራሽ ከተቀጠሩ ጀምሮ በወቅቱ የሴት ተዋናዮች ባለመኖራቸው የሴት ገጸባህሪዎችን ወክለው ጭምር ይጫወቱ ነበር።

በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴ.ቪ. ሲቋቋም የልጆች ጊዜ የተሰኘ ፕሮግራም ሃሳብን አቅርበው በማጸደቅ የልጆች ፕሮግራምን የፈጠራ ክህሎታቸውን በመጠቀም ማቅረብ ጀምረዋል።

ይሄንንው ከኢትዮጵያ ህዝብ ያስተዋወቃቸውን ፕሮግራም ለ42 ዓመታት የራሳቸውን የአቀራረብ መንገድ በመፍጠር በአባትነት ስሜት ለሚሊዮኖች አድርሰዋል።

ለልጆች የተዋዙ ተረቶችን፣ ጨዋታዎችን እና አስተማሪ ዝግጅቶችን በማቅረብ የልጆችን የቅዳሜ ጠዋት ጊዜ አፍክተዋል።

አባባ ተስፋዬ የተለያዩ ሙያዎች ያሏቸው የኪነጥበብ ሰው ነበሩ። ከነዚህም መካከል ተዋናይ፣ ድምጻዊ፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፣ ደራሲ (የልጆች ተረት)፣ ተረት ተናጋሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ ይጠቀሳሉ።

በገና፣ መሰንቆ፣ ክራር፣ አኮርዲዮን፣ ትራምፔት፣ ትርምቦን እና ጃስ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የሚጫወቱ ሲሆን ከዛም በተጨማሪ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጣልያንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋን ተናጋሪ መሆናቸውም ይነገርላቸዋል።

አባባ ተስፋዬ ወደ ደቡብ ኮሪያ ከዘመተው ቃኘው ሻለቃ ጋር አብረው ዘምተዋል። ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የወርቅ ሰአት ተሸላሚ ናቸው። ከዩኘን ሳይቴሽን የአሜሪካ መንግስት ሽልማት አግኝተዋል። በ1991 ዓ.ም. ደግሞ በኪነ ጥበብ ዘርፉ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ናቸው።

በ1973 ዓ.ም. ለ36 ዓመታት ካገለገሉበት ብሄራዊ ቴያትር በጡረታ ተገለዋል። ለ42 ዓመታት ልጆችን ተረትና ምሳሌ በማስተማር፤ የሚታወቁት አንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰው በ1998 ዓ.ም. በኋላ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መቀጠል አልቻሉም።

እኒህ ሰው ታዲያ ያረፉት በ93 ዓመታቸው ሰኞ ሐምሌ 24፣ 2009 ዓ.ም. ነበር።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-01