ሀገሬ ቲቪ

አንድ ህንዳዊ ገላውን ሳይታጠብ 22 ዓመታትን አስቆጠረ

የራስን ጤና ለመጠበቅ እና ከተለያዩ በሽታዎች ለመራቅ ንፅህና ዋነኛው መንገድ ነው። ከዚህም ባለፈ ከከባቢያችን ጀምሮ ዙሪያችን ያሉ ሁሉም ነገሮች ንጹ እና ፅዱ ሲሆኑ ለመንፈሳችን እረፍትን ለአይናችን ደግሞ ያማረ ውበትን ያቀብላሉ።

ታዲያ ይህ ንፅህና መነሻውም መድረሻውም ሰው ነው። ሁሉም ነገር ከራስ ይጀምራል እና ሰው ለራሱ ንፅህና አብዝቶ ይጨነቃል።

ለዚህም ይመስላል በልጅ አእምሮአችን ስለ ስለ ግል ንፅህና በትምህርት ቤት ሳይቀር ተምረነው የምናልፈው። ለዚህ ደግሞ ገላን መታጠብ አንዱ ነው።

እኛ ገላቸውን ሳይታጠቡ ዘመናትን የተሻገሩ አንድ ሰው መኖራቸውን ሰማን እና ወደ እናንተ ልናቀብላችሁ ወደድን። እኚህ ጎልማሳ በህንድ ቢሃር በምትባል አካባቢ ይኖራሉ። ስማቸው ዳራምዴቭ ራም ይባላሉ።

ታዲያ እኚህ የ62 ዓመት ሰው ላለፉት 22 ዓመታት ገላቸውን ውሃ ሳይነካው ዛሬም ድረስ አሉ። እኚህ ሰው ገላቸውን ላለመታጠብ የወሰኑበት አጋጣሚ ደግሞ በርካቶችን አነጋግሯል።

ዳራምዴቭ በሴቶች እና በእንስሳት ላይ የሚፈፀሙ ግፎች እና ግድያዎች እስካልቆሙ ድረስ ገላቸውን ውሃ ላለማስነካት ምለው ውሃን እንደራቁ ይናገራሉ።

ዳራምዴቭ በሚኖርባት መንደር በእርሻ መሬት አስታኮ የተነሳው ብጥብጥ ለበርካ ከብቶች ሞት ምክኛት ይሆናል፣ ከዚህም ባለፈ በአካባቢው በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ከመቀነስ ይልቅ ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ ያሳስባቸዋል።

እሳቸውን የሀይማኖት ትምህርት እያስተማሩ እዚህ ያደረሷቸውን የሀይማኖት አባት (በህንዶቹ እጣራር ጉሩ) ያማችሯቸዋል። ይህ ሁሉ ጥፋት ቆሞ እስካላየው ድረስ ገላዬን ውሃ ላለማስነካት መማላቸውንም ያጫውቷቸዋል።

የሀይማኖት አባትየውም መልካም ነው ይበሉ ይቀጥሉበት ይሏቸዋል። በግዜው የቤተሰብ አስተዳዳሪ የነበሩት ዳራምዴቭ ቤተሰባቸውን ማኖር አለባቸው እና አቋርጠውት ወደነበረው የፋብሪካ ስራ ተመልሰው ይገባሉ።

ታዲያ የፋብሪካው ኃላፊዎች ሰራተኛቸው ስለያዘው ያለመታጠብ ሱባኤ ይሰማሉ። በዚህ ደስተኛ አልነበሩም እና ከስራ አባረዋቸዋል።

ይህ ሁኔታ ታዲያ የእኚህን ሰው ቃልኪዳን አላፈረሰውም፣ በመጀመሪያ ሚታቸው ኋላም ሁለቱ ልጆቻቸው ይህንን ዓለም ተሰናብተው ሲሄዱ እንኳን እንደ ስርዓቱ ገላቸውን ታጥበው ነጭ ለብሰው አልሸኟቸውም፤ በዛው ውሃን በራቀው ሰውነታቸው ነጩን ልብስ ደርበው ሀዘን ተቀመጡ እንጂ።

ምናልባት የዳራምዴቭ 22 ዓመት የበዛ መስሎ ሊሰማን ይችል ይሆናል። ከዓመታት አስቀድሞ በኢራን የሚኖሩ የነበሩ አንድ የ80 ዓመት አዛውንት ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት ውሃ የሚባል ነገር ከመጠጣት በስተቀር በሰውነቱ ላይ አርፎ እንደማያውቅ ተዘግቦ እንደነበር ልናስታውሳችሁ እንወዳለን።

እኚህ ሰው ከስው እርቀው ለብቻቸው መኖርን ምርጫቸው ካደረጉ በኋላ ውሃ እና እሳችውም በዛው ተራርቀው ሲል ዴይሊ ሜል ከዓመታት በፊት አስነብቦ ነበር።

በሳምሶን ገድሉ
2022-08-02