ሀገሬ ቲቪ

32 ሀገራት ኢራቅን እንዲወጉ ምክንያት የሆነችው ዕለት

በታሪክ መካከለኛው ምስራቅ ላይ ስለሆነ አንድ ክስተት እንነግራችኋለን። ነገሩ የሆነው በ1982 ዓ.ም. በዛሬዋ ዕለት ነበር።

በሳዳም ሁሴን አስተዳደር ስር የነበረችው ኢራቅ ገና በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ትንሿን በነዳጅ ዘይት የበለጸገችውን ኩዌት ላይ ጥቃት ከፈተች። ኩዌትን ኢራቅ እንደ ነዳጅ ዘይት ሌባ አይታታለች።

ለስምንት ዓመታት ኢራን እና ኢራቅ ቀደም ብለው ባደረጉት ጦርነት ኩዌት ከኢራቅ ጋር ወዳጅ ነበረች። በጦርነቱ ያበደረችውን የ14 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንዲመለስላት ትፈልጋለች። ኢራቅ ደግሞ የመክፈል አቅም ላይ አልነበረችም።

ኩዌት ብድሩን የመተው ፍላጎት አልነበራትም። በመካከላቸው ያለው ውጥረት ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተደምሮ ተባብሶ ኢራቅ ኩዌትን አጠቃች።

የኩዌት መከላከያ ኃይል ጭንቅ ውስጥ ገብቷል። የተረፉትም ወዳሳኡዲ ሸሹ። ይሄ ዱብዳ የደረሰባቸው የኩዌት መሪዎች ሽሽታቸውን ወደ ሳኡዲ አረቢያ ሆነ። በሰዓታት ውስጥ ኢራቃውያኑ የኩዌትን ከተማ ተቆጣጥረው የራሳቸውን አስተዳደር አቋቋሙ።

ኩዌትን በመያዝም ኢራቅ 20 በመቶ የዓለም የነዳጅ ክምችትን በእጇ አስገባች።

በፐርሽያ የባህር ሰላጤ የባህር ዳርቻ ላይ ኢራቅ ከፍተኛ ቁጥጥሩን ወሰደች። በዚያው ቀን የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ባንድ ድምጽ ኢራቅ ሆይ ኩዌትን ለቀሽ ውጭ ሲል አወገዘ። ግን ኢራቅ ኩዌትን አለቀቀችም ነበር። በዚህም ከቀናት በኋላ የጸጥታው ምክር ቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኢራን ጋር ንግድ ማድረግን ከለከለ።

የአሜሪካ ኃይሎች ወደ ፐርሽያ የባህር ሰላጤ ገሰገሱ። የበርሃው ጋሻ ‘’Desert Shield’’ ተልዕኮም ተጀመረ። የኢራቅ የጊዜው መሪ ሳዳም ሁሴን ግን በተቆጣጠሯት ኩዌት 300 ሺህ ሰራዊት ያለው ጦር ገንብተው ነበር።

ከሶስት ወራት በኋላ የጸጥታው ምክር ቤት በኢራቅ ላይ ኃይል መጠቀምን ፈቀደ። ኃይል መጠቀሙ የሚፈጸመው ግን በ1983 ዓ.ም. ጥር ላይ ኢራቅ ኩዌትን ለቃ ካልወጣች ነው አለ።

ግና ደግሞ ሳዳም ሁሴን ኩዌትን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። የራሳቸው የሆነ የኢራቅ አስተዳደርን ገነቡ። 700 ሺህ የሚደርሱ የህብረት ኃይሎች ኢራቅን ለማስገደድ በመካከለኛው ምስራቅ ተሰባሰቡ። ከነዚህ ኃይሎች በዋናነት አሜሪካውያን ይገኙበታል።

ኢራቅ ከኩዌት እንድትወጣ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ካለፈ ካንድ ቀን በኋል የበርሃው መብረቅ ‘’Desert Storm’’ ተልዕኮ ተጀመረ። ይሄው ተልዕኮ በዋናነት በአሜሪካ የሚመራ ኢራቅ ላይ የተከፈተ ጥቃት ነበር።

የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ለዓለም ቀጥታ እየተላለፈ ባግዳድን ክፉኛ ደበደቡ። ይሄው የበረሃው አውሎ ነፋስ ተልዕኮ በአሜሪካ የሚመራ ቢሆንም ብሪቴይን፣ግብጽ፣ ፈረንሳይ፣ ሳኡዲ አረቢያ እና ኩዌትን ጨምሮ 32 ሀገራት የተሳተፉበት ነው።

በቀጣዮቹ ስድስት ሳምንታት የህብረት ኃይሉ የአየር ጥቃት በኢራቅ ወታደራዊ እና ሲቪል ተቋማት ላይ ተጠናክሮ ቀጠለ። የአየር ጥቃቱ ብዙም መከላከል አልገጠመውም ነበር። የኢራቅ ኃይሎች በውርጅብኙ ረዳት አልባ ሆነዋል።

ሳዳም ሁሴን እንደመፍትሄ እስራኤልን ወደ ጦርነቱ ለማስገባት በሚል ወደ እስራኤል የሚሳኤል ጥቃት እንዲፈጸም አደረጉ። እስራኤል ወደ ጦርነቱ ከገባች የአረቡን ዓለም እገዛ አገኛለሁ በሚል ስሌት ነበር። ግና እስራኤል ወደ ጦርነቱ ሳትገባ ቀረች።

ከበርሃው ማዕበል ተልዕኮ መጀመር አንድ ወር በኋላ የመሬት ጥቃት በኢራቅ ኃይሎች ላይ ተጀመረ። የኢራቅ ኃይሎች ጥቃቱን መቋቋም አልቻሉ። 10 ሺህ የሚደርሱ በአንድ ቀን ውስጥ እጅ ሰጡ። የአሜሪካ የአየር ጥቃት ግን ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።

የመሬት ጥቃቱ በተጀመረ በአራት ቀናት ውስጥ ኩዌት ነጻ ወጣች። የኢራቅ የሰባት ወራት የኩዌት አስተዳደር ጊዜም ተቋጨ። የኢራቅ ኃይሎችም ተማረኩ፣ ሞቱ፣ የተረፉትም ወደ ኢራቅ ሸሹ።

የአሜሪካ የጊዜው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ የተኩስ አቁም አወጁ። ቀጥሎም የጸጥታው ምክር ቤት ጦርነቱ እንዲያበቃ ውሳኔ አሳለፈ። በውሳኔው መሰረት የጆርጅ ቡሽ የተኩስ አቁም ጸደቀ፤ አንዳንድ ማዕቀቦች ተነሱ። ነገር ግን የኢራቅ የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎቿን እስክታወድም ይቀጥል ተባለ።

በዚሁ የፐርሽያ የባህር ሰላጤ ጦርነት በኢራቅ ላይ የደረሰው ጥቃት ምን ያክል ነው የሚለው ጥርት ያለ መረጃ ባይኖርም 25 ሺህ ያክል ወታደሮች እንደሞቱ ብሎም 75 ሺህ የሚደርሱ እንደቆሰሉ ይታመናል።

በታሪክም ውስጥ አንድ ሀገር ብቻዋን የህብረት ኃይሎችን ጦርነት የገጠመችበት አንዱ እና ትልቁ ክስተት ነው። 100 ሺህ የሚደርሱ የኢራቅ ሲቪል ዜጎችም ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የውሃ እና የምግብ እጥረትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሞተዋል።

ኢራቅ የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተቀብያለሁ አለች። ሆኖም በቀጣዮቹ አስር አመታት ስምምነቱ ሳዳም ሁሴን እየጣሱ ነው በማለት የትብብር የአየር ላይ ጥቃቶች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀቦች በኢራቅ ላይ በተደጋጋሚ ተጥለዋል። በተደጋጋሚ በተጣሉት ማዕቀቦች ሳቢያም አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ የኢራቅ ሲቪል ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-02