ሀገሬ ቲቪ

ቻይና ወደ ታይዋን የምትልከውን አሸዋ አቋረጠች

የቻይና እና ታይዋና በድጋሜ ጠንከር ያለ ውጥረት ውስጥ ስለመግባታቸው እየተነገረ ነው። ታይዋን ከቻይና ተገንጥላ የራሷን ሕገ መንግሥት እና ሥርዓተ መንግሥት ከመሰረተች በርካታ ዓመታት አልፈዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቻይና በእር በእርስ ጦርነት ትታመስ በነበረት ወቅት ነው ታይዋን ልትገነጠል የቻለችው።

ከዚያን ዕለት ጀምሮ ቻይና እንደቀድሞ ጊዜ የራሷ አካል ኾና እንድትቀጥል ልዩ ፍላጎት አላት ታይዋን ደግሞ ይህ ፈጽሞ የማይኾን ነው ራሴን የቻልኩ ሀገር እንደኾንኩ ነው መቀጠል የምሻው ስትል ትሞግታለች።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኹለቱ ሀገራትን ጉዳይ ምንጊዜም ከታይ ዋን ጎን እንደሚኾኑ እና ቻይና አንዳች የኀይል እርምጃ የምትወስድ ከኾነ አሜሪካ ዝም ብላ እንደማትቀመጥ መናገራቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትናንትናው ዕለት የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን መግባታቸውን ተከትሎ ታዲያ ቻይና የጦር ልምምድ ወደማድረጉ እንደሔደች ተሰምቷ።

በዛሬው ዕለት ደግሞ የቻይና ንግድ ሚኒስቴር ከታዋን ጋር ባለው የንግድ ትስስር ላይ የተለያዩ ገደቦችን ጥሏል።

የቻይና የንግድና የታክስ ባለሥልጣን ታይዋን ሆይ ከዚህ በኋላ ከኔ የምታስገቢውን አሸዋ ማግኘት እንደማትችይ እወቂ ሲል አሳስቧል።

ታይዋን ለግንባታ ሥራ በርከት ያለ አሸዋን ከቻይና ነው የምታስገባው። በተጨማሪ ፍራፍሬዎችንና የዓሳ ምርቶችን ወደ ታይዋን እንደማትልክ ነው ቻይና ዛሬ ያሳወቀችው።

ከኹለት ዓመት በፊት ታይዋን 5.67 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የተፈጥሮ አሸዋና ጠጠር ከቻይና አስገብታለች። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የታይዋን ወደ ውጪ ከሚገባው አሸዋና ጠጠር የሚገኘው ከቻይና ነው። በ2012 እና 2013 ዓ.ም ከ 70 እስከ 170 ሺህ ቶን የተፈጥሮ አሸዋን ታይዋን ወደ ሀገሯ አስገብታለች።

በየመንደሩ እንደቀላል ነገር የምናየው አሸዋ የቻይና እና የታይዋን ዋንኛ የንግድ ግብአት እባ የፖለቲካ ሁኔታቸውን የሚወስን ምርት ነው።

በተመሳሳይ የቻይና ታይዋን ጉዳዮች ቢሮ ዋናው የቻይና ኩባንያዎችና ግለሰቦች ከሁለት የታይዋን ፋውንዴሽን ወይም ተቋማት ጋር የገንዘብ ግንኙነት እንዳያደርጉ ከልክሏል። እነዚህ ተቋማት የታይዋን የዴሞክራሲ ፋውንዴሽን እና የታይዋን ዓለም አቀፍ ትብብር እና ልማት ፈንድ የተሰኙት ናቸው።

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የቤጂንግን ማሳሰቢያ ችላ ብለው ወደ ታይዋን መግባታቸው ያበሳጫት ቻይና ከታይዋን ጋር ያላትን የንግድ ትስስርን ላይ እገዳ የመጣው የምዝገባ እድሳት ያላደረጉ 100 የታይዋን የምግብ ላኪዎች የላኪነት ምዘገባቸውን አለማደሳቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም አሜሪካ በውጥ ጉዳዮቼ ከልክ በላይ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ቻይና በውጪጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ተነግራለች።

“የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን ሔደዋል። ይህም የቻይናን የውስጥ ጉዳይን በሰፊው የሚጥስ ነው። የቻይናን ሉዐላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ ነው። የአንድ ቻይና መርህን ኾን ተብሎ ለመጣስ የሚደረግ ነው። በታይዋን ሰርጥ ላይ ያለን ሰላም እና ደኅንነትን አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው።”

የታይዋን የምግብና መድሃኒት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዉ ሹ-ማይ በበኩላቸው የቻይና እርምጃ ፖለቲካዊ መነሳሳት ያለው ነው ብለዋል።

ቻይና የታይዋን ትልቋ የንግድ አጋር ናት። በ2013 ዓ.ም ታይዋን ወደ ቻይና 188.9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ልካለች። ይሁን እንጂ ቻይና ንግድን እንደ ጦር መሣሪያ የምትጠቀም ሀገራት የሚል ተደጋጋሚ ስሞታ ይቀርብባታል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-08-03