ሀገሬ ቲቪ

ሶማሊላንድን የወረረው ፋሽስት

በዕለቱን ከታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪካዊ ሁነቶችን እናስቃኛችኋለን። ዛሬ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ስለተከናወነ አንድ ሁነት እንነግራችኋለን። ፋሽስት ጣሊያን የጣሊያን ምስራቅ አፍሪካን የመመስረት ዕቅድ ይዞ ተነስቷል።

ምንም እንኳን ማስተዳደሩ ቀላል ባይሆንለትም እንደሚታወቀው በ1928 ዓ.ም. ሀገራችንን ይዟል። ታዲያ ፋሽስት ጣሊያን ከኢትዮጵያ በመነሳት በ1932 ዓ.ም. በዛሬዋ ዕለት ነበር በብሪትሽ እጅ የነበረውን የሶማሊላንድ ክፍልን መወረር የጀመረው።

የፋሽስት ጣሊያን መሪ የነበረው ሙሶሎኒ በምስራቅ አፍሪካ ጣሊያንን ትልቅ ኃይል የማድረግ ህልም ሰንቋል። ለዚህም ከ40 ዓመታት የአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያን በመውረር በኃይል ያዘ። ጣሊያን በዚሁ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ቀደም ብላም ኤርትራ እና የሶማሊያ ክፍልን ይዛለች።

በ1932 ዓ.ም. ሙሶሎኒ ከሂትለር መወዳጀቱ ደግሞ የልብ ልብ ሰጥቶታል። ምስራቅ አፍሪካን የመጠቅለል ዕቅድ የጣሊያን የምስራቅ አፍሪካ ዘመቻን ወጠነ። በምስራቅ አፍሪካ ኤርትራን፣ ኢትዮጵያን እና ሶማሊላንድን ያቀፈ ትልቅ የጣሊያን ግዛት ለመምስረት አቅዷል።በቀጠናው ከፍተኛ የሆነ የወረራ ፖሊሲንም አወጣ።

ነገር ግን በቀጠናው የእንግሊዝ መነኦር ደግሞ ምስራቅ አፍሪካን የመጠቅለል እቅድ ላለው ሞሶሎኒ እንቅፋት ነበር። ቢሆንም የጣሊያን ጦር በቀጠናው ከነበረው የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ጦር የሚልቅ ነበር።

ለፋሽስት ጣሊያን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከሂትለር በመወዳጀት ከእነእንግሊዝ ውጥረት ውስጥ መግባቱ በምስራቅ አፍሪካ የቅኝ ግዛት ስፍራቸውም ለግጭት ዳርጓቸዋል። የእንግሊዝ ባህር ኃይል በሜዲትራኒያን እና ቀይ ባህር አካባቢ የነበረው የበላይነት የጣሊያን አቅርቦት ላይ ቁጥጥር ይወስዳል የሚል ስጋት ለፋሽስት ጣሊያን አሳድሮበታል።

ይህም ኢትዮጵያን በቁጥጥር ስር አስገብቻለሁ ያለው ሙሶሎኒ ከኢትዮጵያ እና ከጣሊያን ሶማሊላንድ የእንግሊዝ ሶማሊላንድን ወረረ። ይህም የሆነው ከ82 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት ነበር።በተመሳሳይም ፋሽስት ጣሊያን በእንግሊዝ ቁጥጥር ስር በነበሩት ሱዳን እና ኬንያ ላይም ጥቃት ፈጸመ።

የእንግሊዝ ሶማሊላንድን የመውረራቸው ምክንያት ግን የኢትዮጵያ አስተዳደርን ለማጽናት እና ላለመነጠቅ ነበር። አካባቢው በብሪቴይን የጥበቃ ሰራዊት ስር የነበረ ነው። በአካባቢው ከፍተኛ የጣሊያን ባለስልጣን የኦስታ መስፍን ወረራው እንዲጀመር አደረገ። የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የጣሊያን ሶማሊላንድ ኃይሎች ተሳታፊ ሆነውበታል።

የጣሊያን እና የእንግሊዝ ኃይሎች በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በቱግ አርጋን ለውጊያ ገጠሙ። የጣሊያን ኃይሎች በጦርነቱ የበላይነቱን ወሰዱ። ከአፍሪካ እና ከህንድ የተውጣጡት የእንግሊዝ ኃይሎች የፋሽስት ጣሊያን ጥቃት በረታባቸው።

በዚህም የጣሊያን ተዋጊ እና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ተሳታፊ ሆነዋል። የእንግሊዝ ኃይሎች ጣሊያኖች እስኪያጠቋቸው በመጠበቅ የመከላከል አማራጭን ተጠቀሙ። መጀመሪያ ላይ በ2000 የጣሊያን ኃይሎች ላይ ጉዳት ማድረስ ቢችሉም ቁጥራቸው 350 ያክል ነበር። በጣሊያን ኃይሎች የበላይነት ግን ለመሸሽ ተገደዱ።

በርግጥ የጣሊያን ኃይሎች ለወር ያክል የሶማሊላንድ ዋና ከተማ በረበራ አልገቡም። እንግሊዝ የሶማሊላንድ ቅኝ ግዛቷን ለቃ ወጣች። የአፍሪካ ኃይሏን በኬንያ አደራጀች።

በምስራቅ አፍሪካ የሚያደርጉት ጦርነትም ለወራት ተራዘመ። ጣሊያን ኢትዮጵያን መውረር ስትጀመር ኢትዮጵያን ከመደገፍ ድምጿን አጥፍታ የነበረችው እንግሊዝ በዚህኛው ጥቃት በኢትዮጵያ በኩል ጣሊያንን መልሶ ለማጥቃት ተዘጋጀች።

ለዚህ ደግሞ ሀገሩን ከፋሽስት ጣሊያን ለማስለቀቅ እየታገለ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ እገዛ ያደርግላታል።እንግሊዝ በሀገራችን አርበኞች እገዛ ጣሊያንን በኢትዮጵያ መውጋት ጀመረች።

የጣሊያን ኃይሎች ሽንፈት ገጠማቸው ኢትዮጵያንም በ1935 ዓ.ም. ለመልቀቅ ተገደዱ። በሶማሊላንድ የነበሩት የጣሊያን ኃይሎችም እጃቸውን በዚያው ለነበረው የሶማሊላንድ የእንግሊዝ ኃይሎች ሰጡ። የሞሶሎኒ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ግዛት የመምስረት ህልምም አከተመ።

በአብርሃም በለጠ
2022-08-03