ሀገሬ ቲቪ

እግር ኳስን ባልተለመደ ቦታ የሚጫወቱት ጓደኛሞች

በአለማችን በብዙሀን ዘንድ የሚወደድ የስፖርት አይነት ነው ። ለበርካቶች መዝናኛ ፤ ጊዜ ማሳለፊያ እንዲሁም ጤንነት መጠበቂያ ሲሆን ጥበቡን ላደላቸው ደግሞ እንጀራቸው ነው ። ተወዳጁ ስፖርት እግር ኳስ ።

ታዲያ እግር ኳስን ለመጫወት ሲታሰብ አንድ ነገር ያስፈልጋል ። አቀማመጡ የተስተካከለ ሜዳ ። በ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለጨዋታው ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ባለመኖራቸው ብዙዎች በተሽከርካሪ መንገዶች እንዲሁም አመቺ ባልሆኑ ስፍራዎች ሲጨዋቱ ይስተዋላል። ይህም የሆነው ለስፖርቱ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ነው ።

ዛሬ ስለ እግር ኳስ የመጨዋጫ ሜዳዎች ያነሳንላችሁ ያለምክንያት አይደለም ። ከወደ ኦስትሪያ እግር ኳስን ባልተለመደ ቦታ የሚጫወቱ ሰዎችን ልናስተዋውቃችሁ ነው።

በ ኦስትሪያ የሚገኙ ጓደኛሞች የሚወዱትን የ እግር ኳስ ጨዋታ ለረጅም አመታት በአካባቢያቸው በሚገኘው የአልፕስ ተራራ ላይ እንደሚጫወቱ ኦዲቲ ሴንትራል በፊት ገጹ ላይ አስፍሮታል ።

ይህን ያልተለመድ የአጨዋወት አይነትም የአልፓይን እግር ኳስ ሲሉ ሰይመውታል ። እኚህ ጓደኛሞች ሁለት ጎሎችን በተራራው ጫፍና ጫፍ በመስራት እንኳን ለመሮጥ ለመራመድ አስቸጋሪ በሆነ ቦታ ላይ የሚወዷትን ኳስ ያንከባልሏታል።

እግር ኳስ አንዱ በአንዱ ላይ ጎል በማስቆጠር ከማሸነፍ ወጪ ውበቱን በማጣቱ ይህን አይነት የ አጨዋወት መንገድ እንደፈጠሩ የሚናገሩት ጓደኛሞቹ ለዚህም ምክንያታቸው በ 2014 የ ዐለም ዋንጫ ወቅት የተመለከቱት አሰልቺ ጨዋታ እንደሆነ ይናገራሉ ።

የአልፓይን እግር ኳስ ልክ እንደ ትክክለኛው ሜዳ መስመሮች ተሰምረውለት በ እግር ኳስ ህግና ደንብ ቢመራም መሸወድ ወይም ጥበቦችን ማሳየት ግን አይታሰብም ኳስ እግር ላይ እንደገባ ለቡድን አጋር አቀብሎ መንከባለል እንጂ ።

ይህም ብዙዎችን ከማዝናናቱ ውጪ ለተጫዋቾች አያሌ የ ጤና ጠቀሜታን አስገኝቷል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል ።

በዮሴፍ ከበደ
2022-08-03