ሀገሬ ቲቪ

ያለ ሰው ዕገዛ የሚሰራው የቴሌኮም ማሽን በመዲናችን

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ያለሰው እገዛ የሚያስተናገዱባቸው ማሽኖች በአዲስ አበባ መትከሉን ገለጸ፡፡ ተጠቃሚዎች እነዚህን ማሽኖች በመጠቀም የአየር ሰዓት መሙላት፣ አዲስ ሲም ካርድ ማውጣትና የመስመር ስልክ ቢል መክፈል ይችላሉ፡፡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችሉ አሥር ‹ሰልፍ ሰርቪንግ› ማሽኖችን ናቸው የተለያዩ ቦታዎች የተተከሉት፡፡ ማሽኖቹ በቦሌ፣ በቸርችል፣ በካዛንቺስ፣ በጊዮርጊስ፣ በለቡና ሌሎች የኢትዮ ቴሌኮም ቅርንጫፎች ያሉባቸው አካባቢዎች መተከላቸውን ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡ በ2014 ደንበኞቹን 64 ሚሊዮን የማድረስ ዕቅድ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም በዚሁ ዓመት የ5ጂ ኔትወርክ የማስጀመርና በተመረጡ ቦታዎች ላይ 24 ሰዓት የሚሠሩ ቅርንጫፎችን የመክፈት ሐሳብ አለው፡፡ ደንበኞች ማሽኑ ውስጥ ገንዘብ በማስገባት ስልካቸው ላይ የአየር ሰዓት እንዲሞላ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በማሽኖቹ ላይ አዲስ ሲም ካርድ ለማውጣት የሚያስፈልጉ መረጃዎች መሙላትና ፎቶግራፍ መነሳትም እንደሚቻል ተገልጿል፡ ከዚህም በተጨማሪ የቴሌ ብር ተጠቃሚዎች ማሽኖቹን በመጠቀም ገንዘብ ማውጣትና ማስገባት የሚችሉበትን አማራጭ በማካተት፣ የማሽኖቹን ሥራ ለማስጀመር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተተከሉት አሥር ማሽኖች ላይ የሚደረገው የሶፍትዌርና የሌሎች የቅድመ ሙከራ ሥራዎች ሲጠናቀቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር የባንክ የክፍያ ማሽኖችን (ኤቲኤም) በመጠቀም የአየር ሰዓት መሙላት ለማስቻል ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለመዘርጋት በስራ ላይ ነው፡፡

በሀገሬ ቲቪ
2021-12-22